top of page

ግንቦት 26፣2016 - የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስረኞችን በሃገራዊ ምክክሩ ለማሳተፍ እየሰራሁ ነው አለ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በህግ ጥላ ስር የሚገኙ እስረኞችን በሃገራዊ ምክክሩ ለማሳተፍ እየሰራሁ ነው አለ፡፡


በምክክሩ ሂደት አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ላይ የሚገኘው ኮሚሽኑ በተቻለ መጠን ሁሉም ይሳተፋል፤ አንድም የሚቀር የማህበረሰቡ ክፍል የለም ብሏል፡፡


ሁሉም ተሳታፊ፤ ለምክክሩ ይበጃል ሊመከርበትም ይገባል የሚለውን አጀንዳ እያቀረበም ይገኛል፡፡


በተለያዩ ምክንቶች ተጠርጥረው የታሰሩ፤ በተለይም በፖለቲካ እንቅስቃሴቸው ምክንያት የታሰሩ ፖለቲከኞች በአካል ወደ ምክክሩ መጥተው መሳተፍ ስለማይችሉ፤ በምክክሩ እንዴት ይሳተፉ የሚለውን እየተነጋገርበር ነው ያሉን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድህን ናቸው፡፡


በተጨማሪም ኮሚሽነሯ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ነገር ግን በአጀንዳነት ይያዝልን የሚሉት ሃሳብ ያላቸው እስረኞች አጀንዳቸውን ከእስር ቤት ሆነው እንዲልኩ ለምን አልተደረገም በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፣ እስረኞቹ በምን መንገድ ይሳተፉ የሚለው ገና አልተወሰነም እየተመከረበት ነው፤ ነገር ግን ሃሳቦቻቸው በፓርቲዎቻቸው በኩል ይካተታሉ ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ካሳለፍነው ግንቦት 21 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታ 7 ቀናት በአዲስ አበባ ሲያካሂድ የቆየው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በነገው እለት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


ምንታምር ፀጋው



Comments


bottom of page