top of page

ግንቦት 26፣2016 - በኢትዮጵያ ከ7 ሚሊዮን በላይ ገበሬ መኖሪያ መተዳደሪያው ጤፍ እንደሆነ ይጠቀሳል

ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ገበታ የማትጠፋው ጤፍ፤ በምርት ሂደት ዋነኛ ችግሯ የሆነውን ግሽበት ወይንም መውደቅን ለመከላከል ያለመ ምርምር ተደርጎ ውጤትም መገኘቱ መነገሩ ይታወሳል፡፡


ምርምሩ የተደረገው በአሜሪካ ሀገር ‘’Donald Danforth Plant science Center’’ በተባለ የእፀዋት ምርምር ማዕከል ሲሆን፤ የጤፍ ግሽበትን ለማስቀረት ጥቅም ላይ የዋለው ምርምርም፤ ‘’ጄኔሞ ኤዲቲንግ’’ ወይም ‘’ጂን ኢዲቲንግ’’ የሚባል ነው፡፡


በጤፍ ላይ በተደረገው በዚህ ጂን አዲተንግ፤ የጤፍን ግሽበት (መውደቅን) መከላከል ተችሏል፤ ምርታማነትንም በ25 በመቶ ማሳደግ ይቻላል ሲል ውጤቱ አሳይቷል፡፡


ሰርገኛ፣ ማኛ እየተባለች የምትጠራው ለእንጀራም፣ ለዳቦ፣ ለገንፎም ለሌላውም የምትሆነው ጤፍ ላይ የተደረገውን ምርምር ላይ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ምንድነው ከምርምሩ በኋላስ ምን እየተሰራ ነው፣ ምንስ ለመስራት ታስቧል?


ሸገር በዚህ ጉዳይ ላይ በጤፍ ላይ ምርምሩ ሲደረግ አብሮ የሰራውን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን ጠይቋል፡፡


የምርምሩ ውጤት ተስፋ ሰጪ ሆኖ በመገኘቱ አሜሪካ ያሉ ሳይንቲስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ተደርጓል ሲሉ በኢንስቲትዩቱ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክተሩ ደጀኔ ግርማ(ዶ/ር) ነግረውናል፡፡


"እዛ ያለው (አሜሪካ ) የምርምር ማዕከል የጤፍ ኮሌክሽን እንዳለው እንዲሁም ከዛ ወስደው እንዳደረጉት ተናግረዋል ደጀኔ ግርማ(ዶ/ር)፡፡


ኤዲት ሲደረግ ግሽበት በመገኘቱ ጤፍ በመውደቁ እሱን ቀና ለማድረግ ታሳቢ መደረጉንና ያነሱት ዳይሬክተሩ ‘’ኤዲት አድርገን ላይኖቹን ስናያቸው ቀጥ ብለው ቆመዋል፣ያልተደረጉት እንደተለመደው ተኝተዋል’’ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፤ ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ እንደሚፈልግ አስረድቷል፡፡


የሀገር ውስጥ አቅም ግንባታ እንዲደረግ መሻቱን ተናግሯል፡፡


ለዚህ መሻቱ ማስፈፀሚያም ከ’’ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን’’ 5 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ሲሉ ተመራማሪው ነግረውናል፡፡


በዚህ ገንዘብ ኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች ወደ አሜሪካ ተጉዘው ስለ ምርምሩ ስልጠና እንዲወስዱ፤ በሀገር ቤት በ’’ሆለታ ግብርና ምርምር’’ በዘርፉ ጥናት እና ምርመራ ለማድግም ታስቧል።


የምርምር ውጤቱ በሀገር ቤት ተጨማሪ የምርምር ስራ የሚጠብቀው ሲሆን በውጤት የሚዘልቅ ከሆነ የዘር ብዜቱ የሚደረገው እዚሁ ይሆናል ተብሏል።


ይህንን በጤፍ ላይ የተደረገውን ምርምር ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ምርምሩን ለመቀጠልም ሆነ ሌሎች ስራዎች ለመቀጠል ግን የአካባቢ ጥበቃ ባለስጣን ፍቃድ እንደሚያስፈልገው ሰምተናል፡፡


በጤፍ ላይ የተደረገው ምርምር፤ የሀገር በቀል ዝርያ ተወሰደ የሚያስብል የሌለበት ነው ያሉት ተመራማሪው፤ ካለም በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መሰረት የሚፈታ ይሆናል ብለው አስረድተዋል።


ተመራማሪው፤ "አሜሪካ ኤዲተ ተደርጎ የተገኘው ውጤት ላይ ኢትዮጵያ የባለቤትነት ጥያቄ ላንሳ ብትል መብት የላትም፤ ምክንያቱም ከእኛ አይደለም ዘሩን ወስደው ኤዲቲንጉን የሰሩት’’ ብለዋል፡፡


‘’እኛ ግን በጣም ስማርት ሆነን ጤፍ ለእኛ አስፈላጊያችን ስለሆነ እንተባበር እና ቴክኖሎጂውን ወደ ኢትዮጵያ እናምጣው፣ ተመራማሪዎቻችንን አቅም ገንቡልን፣አሰልጥኑልን ብለን ነው ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ገንዘብ የሰጠን’’ ሲሉም አክለዋል።


የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙንም ተናግረዋል።

የተገኘው ውጤት የእነሱ መሆኑን የሚጠቅሱት ደጀኔ ግርማ(ዶ/ር) ነገር ግን የትኛውም አይነት ኮሜርሻላይዜሽን ቢኖር ጤፍ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እህል ስለሆነ የሆነ ፐርሰንት ከሚገኘው ገቢ ላይ ለኢትዮጵያ እንዲደረግ የሚል ስምምነት በሰነዱ ውስጥ መካተቱን አስረድተዋል፡፡


በኢትዮጵያ ከ6 ሺህ በላይ የጤፍ ዝርያዎች እንዳሉ የሚነገር ሲሆን፤ በአሜሪካ፣ በጣሊያን፣ በጀርመን፣ በሩሲያም የጤፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡


ጤፍ በተለያየ አለም ተበትኖ ሳለ፤ ጤፍነትን አንሰጥም የሚል ነጠላ ክርክር በጊዜው ብዙ የሚያስጉዝ አይደለም ይላሉ ዶ/ር ደጀኔ።


ብዙ ዓይነት ሆና ከገበታ የምትቀርበዋ ጤፍ፤ ፈላጊዋም እየጨመረ መጥቷል፡፡


በኢትዮጵያ ከ7 ሚሊዮን በላይ ገበሬ መኖሪያ መተዳደሪያው ጤፍ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡


ንጋቱ ሙሉ






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page