top of page

ግንቦት 24፣2016 - እውነት እነዚህ ጠበቆች ለተጠርጣሪው ነፃ መውጣት ይታገላሉ?መንግስት በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሮ ክስ ለሚመሰርትባቸው ግለሰቦች በነፃ ጠበቃ የማቆም ግዴታ እንዳለበት ህግ ያዛል።


በርግጥ በነፃ ጠበቃ የሚያቆመው የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ተጠርጣሪዎች እንጂ ለሁሉም አይደለም።


አንድ ተጠርጣሪ የገንዘብ አቅም የለኝም ካለ ለማረጋገጥ የሚጠበቅበት ፍርድ ቤት ቀርቦ ቃለ መሃላ መፈጸም ብቻ ነው።


ጠበቃው ከዚያ በኋላ ከተከሳሹ ጎን በመቆም ደመወዝ የሚከፍለውን መንግስት መሞገት ይጠበቅበታል።


ይህንኑ ስራ የሚሰሩ 90 ተከላካይ ጠበቆች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር በሚገኘው ‘’የተከላካይ ጠበቆች ፅህፈት ቤት’’ ተመድበዋል።


እውነት ግን እነዚህ ጠበቆች ልክ በተከሳሾች ገንዘብ ተከፍሏቸው እንደሚቀጠሩት ለተጠርጣሪው ነፃ መውጣት ይታገላሉ ?


ደመወዝ ከፋያቸው የሆነውን መንግስትስ በብርቱ የመሞገት ድፍረት አላቸው ወይ ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።


እኛም እነዚህኑ ጥያቄዎች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ለሆኑት አቶ ደሳለኝ ከበደ አቅርበናል።


ከተከላካይ ጠበቃቸው አንዱ የስራ አስፊፃሚው አካል የሆነውን አቃቤ ህግ ከሶ ለተጠርጣሪው ካሣ ያስከፈለበት ጊዜ እንዳለ የነገሩን ሃላፊው፤ ይህን የትኛውም ተቋም እና ግለሰብ አድርጎት አያውቅም ብለዋል።


በመንግስት የሚመደቡ ተከላካይ ጠበቆች በግል ከሚቆሙት ያነሰ ወይም የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ ? የሚለው፤ በገለልተኛ ተቋም ቢጠና ደስ ይለናል የሚሉት ሃላፊው እኛ ግን አፋችንን ሞልተን የምንናገርበት ጉዳይ ነው ብለዋል።


ሰዎች ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ ብቻ ሳይሆን በፖሊስ ምርመራ ስርም እያሉ የህግ ድጋፍ የሚሰጧቸው፤ ባለሞያዎችን በነፃ እንዲያገኙ የማድረግ ዕቅድ እንዳለ ከዚህ ቀደም ተነግሮ ነበር።


ይህስ ጉዳይ ከምን ደረሰ? ብለን የጠየቅናቸው አቶ ደሳለኝ፤ ኢትዮጵያ ይህን እንድታደርግ አጽድቃ የህጓ አካል ያደረገቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ጭምር ያስገድዳሉ፤ ምርመራውን የሚያከናውነው ክፍል ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ ግን ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ሲሉ መልሰዋል።


በምርመራ ወቅት የህግ ድጋፍ የሚሰጡ ሞያተኞች ከተከሳሾች ጋር እንዲሆኑ አለመደረጉ፤ ቀጥሎ በሚመጣው ስራ ላይም ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ አቶ ደሳለኝ ያነሳሉ።


እናንተም የመንግስት አካል ናችሁ፤ በምርመራ ወቅት የመብት ጥሰት ከፈጸሙበን ሰዎች የተለያችሁ አይደላችሁም እየተባልን ነው ብለዋል።


ጽህፈት ቤቱ የሚመድባቸው ተከላካይ ጠበቆች የህግ ድጋፍ የሚሰጡት ጉዳያቸው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ለሚታይ ተከሳሾች እንደሆነ አቶ ደሳለኝ ነግረውናል።


የሚሰጧቸው አገልግሎቶችም የህግ ምክር ፤ የህግ ክርክር ሰነዶች ዝግጅት እና ተገልጋዮችን ወክሎ የችሎት ክርክርት ማካሄድ ናቸው ብለዋል።


ንጋቱ ረጋሣየሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw


Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio


Website: https://www.shegerfm.com/


Comments


bottom of page