ግንቦት 20 2017 - ታሪክን የኋሊት - ኢህዴግ ስልጣን የያዘበት ቀን ግንቦት 20 1983 ዓ/ም
- sheger1021fm
- May 28
- 2 min read
የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ ወታደራዊውን ደርግ አባርሮ የመንግስትን ስልጣን የያዘው በዛሬዋ ቀን ግንቦት 20 1983 ዓ/ም ነበር፡፡
በ1966 ዓ.ም የተቀጣጠለውን የህዝብ አመፅ፣ በጠለፋ መውሰዱ የሚነገርለት የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ወታደራዊ መንግስት፣ ለ17 ዓመቶች በስልጣን ላይ ቆየ፡፡
ስልጣን ከያዘ ከሁለት ወሮች ጀምሮ፣ ግድያን መፍትሄ አድርጎ ይመራ የነበረው፣ የጥቂት መኮንኖችና የበታች ሹማምንት የታደሙበት ወታደራዊ ደርግ፣ እያደር ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ገጠመው፡፡
በሚከተለው ርዕዮተ አለም አስገዳጅነት፣ በሚወስደው የግድያ የእስርና የማሰቃየት ርምጃ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ፣ በትጥቅ ትግል ለመቃወም ፣ ጠመንጃ አንስተው ወደጫካ እንዲገቡ አስገደዳቸው፡፡
ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም የሚመሩት ወታደራዊ ደርግ፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖችን አቅርቦ ሌሎቹን አስገደላቸው፣ እርስ በእርስ እንዲፋጁም የእብድ ገላጋይ ሆኖ ጎራዴ አቀበላቸው፡፡
ተራማጆች ናቸው የሚባሉት ተፋጅተው ሲጨርሱ፣ አቅርቦአቸው የነበሩትን ጭምር እየመነጠረ፣ ለሞትና አሰቃቂ ለእስር ዳረጋቸው፡፡
የሃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር ባለውለታ አዛውንቶች፣ ምሁሮች ተገደሉ፣ ታሰሩ፡፡
ተቀናቃኞቻቸውን የደረግ አባላት ጭምር ቀድመው እያስወገዱ ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ፣ በደርግ ውስጥ በልጠው በመውጣት በሙሉ ስልጣን ሃገራቱን ለመምራት ቻሉ፡፡
አብረዋቸው ከጀመሩት ጓደኞቻቸው ጀምሮ የደርግ አባላትን ፣ የጦር አዛዦችን ጭምር በመረሸናቸው ፣ በፍርሀት እንጂ ወዶ የሚደግፋቸው ጠፋ፡፡
በቀጥታና በተዘዋዋሪም የሚመሩት ፓርቲያቸውን ኢሰፓን ለማስወገድ ከውስጥም በውጭም ትግሉ ተጠናከረ፡፡
የትጥቅ ትግል ከጀመሩት መሀከል ፣ ሕውሀት ከግዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በወታደራዊው መንግስት ላይ ድል እየተቀዳጀ ፣ የነፃ መሬቱን አሰፋ፡፡
የትጥቅ ትግል ከጀመረው ኢህድንም ጋር ፣ ግንባር ፈጥሮ ኢህአዴግን መሰረቱ ፤ ጦርነቱንም አፋፋሙት፡፡
በተለይም የደርግ 604ኛ ኮር ፣ ሽሬ ላይ ከተደመሰሰ በኋላ፣ የሃይል ሚዛኑ ወደ ኢሕአዴግ አዘነበለ፡፡
ለአላማውና ለእምነቱ ፀንቶ የታገለውና ድልን እየቀመሰ የሄደው የኢህአዴግ ሰራዊት ፣ ባላቋረጠ ጦርነት የተዳከመውንና በሽንፈት ሞራሉ ያዘቀዘቀውን የደርግ ሰራዊት እያሸነፈ ፣ ወደ አዲስ አበባ ገሰገሰ፡፡
በ1983 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ፣ ጎንደር፣ ጎጃምና ምዕራብ ሸዋ በኢህአዴግ እጅ ገቡ፡፡ አዲስ አበባም ተከበበች፡፡
የኢህአዴግ ተዋጊ ሠራዊት ደሴን ደብረማርቆስን ሲቆጣጠርና እንደተቃረባቸው ሲያውቁ “በለው ግደለው” እያሉ ሲፎክሩ የነበሩት ጠቅላይ ጦር አዛዡ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ሰራዊቱን በትነው ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በድብቅ ወደ ዚምባብዌ ሸሹ፡፡ የኢህአዴግ የድል እርምጃም ተፋጠነ፡፡
ኮሎኔል መንግስቱን በፕሬዝዳንትነት የተኩዋቸው ፣ ሌፍተናት ጄኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን የተናጠል የተኩስ አቁም ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ግን ውጤት አላመጣም፡፡
በአሜሪካን አደራዳሪነት በሎንደን ተሰብስቦ የነበረው የሻዕቢያ፣ የኢሕአዴግ፣ የኦነግና የደርግ ኢሰፓ፣ ድርድር ያለውጤት ተጠናቀቀና ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንዲይዝ በጉባኤው ተወሰነ፡፡
ማክሰኞ፣ ግንቦት 20/1983 ንጋት ላይ ኢህአዴግ የምንሊክን ታላቁ ቤተ-መንግስትን ተቆጣጠረ፡፡ ብዙ የረባ ተቃውሞ ሳይገጥመው የኢትዮጵያ ሬዲዮን ይዞ ፣የድሉን ወሬ አበሰረ፡፡
በጥቂት ግዜ ፣ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ ሙሉ በሙሉ ሀገሪቷን ተቆጣጠረ፡፡ የደርግ ሹማምንትንም አሰረ፡፡ ይሄ ከሆነ ዛሬ ልክ 34 ዓመት ሆነ፡፡
እሸቴ አሰፋ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
Comments