top of page

ግንቦት 20 2017 - በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከሰራተኞች መብት ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ስራዎች መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተናገረ

  • sheger1021fm
  • May 28
  • 2 min read

በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከሰራተኞች መብት ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ስራዎች መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተናገረ።


ሠራተኞች በማህበር እንዳይደራጁ ከልክለዋል በተባሉ የአዳማ እና ሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚገኙ ሰራተኞች አሁን ላይ ጠንካራ ማህበር ማቋቋማቸውን ኮርፖሬሽኑ አመልክቷል።


የመኖሪያ ቤት እና የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እንዲፈታም በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከሚሰሩ ባለሃብቶች ጋር ንግግር መጀመሩን ሠምተናል።


ቀደም ሲል የኢንዱስትሪ ዞን በነበሩ እና አሁን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በተቀየሩ ተቋማት ሰራተኞች ላይ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ ሲነገር ቆይቷል።


ለሰራተኞቹ የሚከፈለው ደመወዝ እጅግ ዝቅተኛ መሆን ፤ በማህበር እንዳይደራጁ መከልከል እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ይፈጸማሉ የሚሉት ይጠቀሳሉ።


ጉዳዩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሣምንታት በፊት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ባደመጠበት ወቅትም የተነሳ ነበር።


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በበኩሉ ከሰራተኞች መብት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች እንዲፈቱ ጥረቶች መጀመራቸውን ተናግሯል።


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ እንዳሉት ፤ ችግር አለባቸው የተባሉ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ተለይተው የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ነው።


ሠራተኞች በማህበር እንዳይደራጁ ተከልክለዋል የተባሉ የአዳማ እና ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን ላይ ጠንካራ ማህበር አቋቁመዋል ብለዋል።


በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ላይ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች የሚያገለግሉት በዝቅተኛ የስራ መደብ ላይ እንደሆነ የሚገለጽ ነው።


ነገሩ እውነት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዘመን አሁን ግን ብቃታቸው እየታየ በመካከለኛ ደረጃ ባሉ የስራ መደቦች ላይ ፤ በሃላፊነት ቦታ የሚመደቡ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እየታዩ ነው ብለውናል።


በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚገኙ ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ፤ የትራንስፖርት እና የምግብ አቅርቦት ችግሮች እንዳሉባቸው ይነሳል።


ስለዚሁ የጠየቅናቸው አቶ ዘመን መኖሪያ ቤት ለሰራተኞቻቸው የገነቡ ፤ እንዲሁም የምግብና የትራንስፖርት አገልግሎት ፤

ለሰራተኞቻቸው የሚያቀርቡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እንዳሉ ጠቅሰው የእነሱን ልምድ ወደ ሌሎቹም ለማስፋት እየሰራን ነው ብለዋል።


አስሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና ሶስቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአጠቃላይ ከሶስት መቶ ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች፤ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የስራ ዕድል ፈጥረዋል ተብሏል።


ንጋቱ ረጋሣ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Commenti


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page