top of page

ግንቦት 19፣2016 - የዓለም ጤና ድርጅት ያጸደቀው አለም አቀፍ የወረርሽኝ ስምምነት ለታዳጊ ሀገራት ሚዛናዊ ያልሆኑ ጉዳዮች የተካተቱበት ነው ተባለ

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ያጸደቀው አለም አቀፍ የወረርሽኝ ስምምነት ሰነድ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ሚዛናዊ ያልሆኑ ጉዳዮች የተካተቱበት ነው ተባለ።


ኤድስ ሔልዝኬር ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ እና የሲቪል ማህበራት አጋሮቹ በወቅታዊው የዓለም ጤና ድርጅት አለም አቀፍ ወረርሽኝ የስምምነት ሰነድ ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ በሰጡበት ጊዜ ነው እንዲህ የተባለው።


በመግለጫውም የአለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ የስምምነት ሰነድን እንዲያሻሽል ፣ ፍትሃዊ እና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆንም ተጠይቋል።


ለዚህም በ77ኛው የአለም ጤና ጉባኤ ላይ በጤና ሚኒስቴር በኩል እየተሳተፈች ያለችው ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ያካተተ ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ ስምምነት ሰነድ እንዲኖር በጉባኤው መጠየቅ አለባት ተብሏል፡፡


የዓለም ጤና ድርጅት አለም አቀፍ የወረርሽኝ ስምምነት ዓለም አቀፋዊ ዝግጁነትን እና ለተላላፊ በሽታዎች ምላሽን ለማጠናከር ያለመ ማዕቀፍ ቢሆንም የስምምነቱ ውሎች ብዙ ጥያቄዎች የሚያስነሱ ናቸው ተብሏል።


ሰነዱ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ የሚያስፈልጉ የጤና ምርቶች 10 በመቶ በነጻ እና 10 በመቶ ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የቀረውን ደግሞ ለውድድር በማቅረቡ ምክንያት ታዳጊ ሀገራትን ለከፍተኛ እጥረት የሚዳርግ እንደሆነ ተነግሯል::

ይህም የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉንም አባል ሀገራት በእኩል አይን የማየት እና ለታዳጊ ሀገራት ምንም አይነት እገዛ የሌለው መሆኑን ያሳያል ብሏል መግለጫው።


በኮቪድ-19 ወቅት በባለጸጋ እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የሞት እና ህመም ምጣኔ አለመመጣጠን እንዲቀጥሉ ያደርጋል ተብሏል።


ያደጉ ሀገራት ክትባቶችን እና የህክምና መሳሪያዎችን ሚዛናዊ ባልሆነ ሁኔታ የሚያከማቹ በመሆኑ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ደግሞ ለከፍተኛ እጥረት መጋለጣቸው ተጠቅሷል።


በተጨማሪም ስምምነቱ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ሁሉም ሰው የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ከማድረግ ይልቅ የመድሃኒት እና ህክምና መገልገያ ግብአቶች ማምረቻ ኩባንያዎች መብት ያስጠብቃል ተብሏል ።


ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎቿ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰራች ቢሆንም የአለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ ስምምነት ይህንን አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ተጠቅሷል።


መንግሥት ለዜጎች ጤና መብት እንዲቆም እና የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ ስምምነት እንዲያሻሽል ግፊት ማድረግ አለበት መባሉን ሰምተናል።


ምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw


Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio


Website: https://www.shegerfm.com/


Comentários


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page