top of page

ግንቦት 15፣2016 - ስፔናዊው ዜጋ የተገደለው በሁለቱ ብሔረሰቦች የጎሳ አባላት መካከል በተነሳ ግጭት ሰበብ አይደለም ሲል የአሪ ዞን ተናገረ

  • sheger1021fm
  • May 23, 2024
  • 1 min read

ስፔናዊው ዜጋ የተገደለው በሁለቱ ብሔረሰቦች የጎሳ አባላት መካከል በተነሳ ግጭት ሰበብ አይደለም ሲል የአሪ ዞን ተናገረ፡፡


በማጎ በሔራዊ ፓርክ ውስጥ በተከፈተ ተኩስ አንድ ስፔናዊ ዜጋን ጨምሮ 4 ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡


ሰዎቹ የተገደሉት ከትናንት በስቲያ ግንቦት 12 ቀን፤ በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ሰሜናዊ ክፍል የፎቶ ቀረፃ እያካሄዱ በነበረነት ወቅት ነው ተብሏል፡፡


ጥቃቱ በተሰነዘረበት ወቅት በቦታው የነበሩ ሌሎች 10 የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ጂንካ ከተማ እንደገቡ ተነግሯል፡፡

ጥቃቱ ያደረሱት የታጠቁ አካላት እንደሆኑና የመንግስት የፀጥታ አካላት ጥቃት አደራሾቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰሩ እንደሆነ የአሪ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሀላፊ ታምራት ተስፋዬ ለሸገር አስረድተዋል፡፡


በጥቃቱ የተገደለው ስፔናዊው ቶኒ ኢስፓዳስ የተባለ የ’’ካታሎን የቱሪዝም ድርጅት’’ ፎቶ አንሺ እንደነበረ የስፔን መገናኛ በዙሀን ዘግበዋል፡፡


የፎቶ ባለሞያው ከ 20 ዓመታት በላይ የተለያዩ ዶክመነተሪዎችን በመቅረፅ ለሌላው አለም አሁን የተገደለበት አካባቢ እና ኢትዮጵያን ሲያስተዋውቅ የነበረ እንደሆነም ተነግሯል፡፡


ይህ ጥቃት የውጭ ዜጎችን ያነጣጠረ እንዳልነበረ የጠቀሱት አቶ ታምራት፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ እንደተወራውም ተኩሱ የተደረገው በሁለቱ(በአሪ እና በሙርሲ ጎሳ አባላት) በተነሳ ግጭት ምክንያትም አይደለም ብለዋል፡፡


ገዳዮቹ ምን ዓላማ ይዘው ጥቃቱን እንደፈፀሙ በተጨባጭ ባይታወቅም፤ በአካባቢው መሽገው በተለያዩ ጊዜያት የአርሶ አደሮችን ከብትና ንብረት እየዘረፉ የሚወስዱ የተደራጁ ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ ብለውናል፡፡

ከጥቃቱ በኋላም የሟቾችን አስክሬን ለመውሰድ ከጥቃት አደራሾቹ ጋር ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ መደረጉንም አቶ ታምራት አስረድተዋል፡፡


ማጎ ብሄራዊ ፓርክ በደቡብ ኢትዮጵያ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በአሪ ዞን እና በደቡብ ኦሞ ዞን አዋሳኝ የሚገኝ ነው፡፡

በፓርኩ ውስጡ 83 አጥቢ፣ 237 የአአዋፋት እና 14 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች እንደሚገኙበት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡


 ማንያዘዋል ጌታሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page