ግንቦት 14 2017 - የኢትዮጵያ ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች እንዲያስከፍሉ የተቀመጠው ጣሪያ
- sheger1021fm
- May 22
- 2 min read
ባንኮች ለሚሰጧቸው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች የሚያስከፍሉት ገንዘብ ከአራት በመቶ እንዳይበልጥ ተወስኗል።
ውሳኔው ጥሩ የሚባል ቢሆንም የኢትዮጵያ ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች እንዲያስከፍሉ የተቀመጠው ጣሪያ አሁንም ቢሆን ትንሽ እንዳልሆነ አንድ የምጣኔ ሃብት ባለሞያ ተናግረዋል።
ወደ ውጪ ሀገር ለሚሄዱ የግል ተጓዦች የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ወደ አስር ሺህ ዶላር እንዲያድግ የተላለፈው ውሳኔም የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር ይሁን ከመባሉ ጋር የተገናኘ ነው ብለዋል።
ባንኮች ለሚሰጧቸው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች የሚያስከፍሉት ገንዘብ ከአራት በመቶ እንዳይበልጥ መወሰኑን ብሄራዊ ባንክ ይፋ አድርጓል።
ጥቃቅን የአገልግሎት ወጪዎችን ደግሞ እንዲያስቀሩ መወሰኑን ባንኩ ይህንኑ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።
ባንኮች ለሚሰጧቸው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች የሚያስከፍሉት ገንዘብ እስከ አስር በመቶ ደርሶ እንደነበር የሚያስታውሱት፤ የምጣኔ ሃብት ባለሞያው ቴዎድሮስ መኮንን(ዶ/ር) ይህም ከሌሎች ሀገራት አንጻር ከፍተኛ የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።
በሌሎች ሀገራት ለመሰል አገልግሎቶች በባንኮች የሚጠየቀው ክፍያ ከአንድ እና ሁለት በመቶ አይበልጥም ብለዋል።
ከሌሎች ሀገራት አንጻር የአሁኑ ውሳኔም ለባንኮች ጥሩ የሚባል ነው እንደሆነ ነግረውናል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር እንዲሆን በተወሰነበት ወቅት አብዛኞቹ ባንኮች ካላቸው የውጭ ምንዛሪ ሃብት ይልቅ ዕዳቸው ይበልጥ ስለነበር እና ፤ይህም ኪሳራ ውስጥ የሚከታቸው በመሆኑ ያን ለማካካስ ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች ከፍተኛ ገንዘብ ሲጠይቁ ቆይተዋል ብለዋል ዶክተር ቴዎድሮስ።
ከፍተኛ የነበረው የአገልግሎት ዋጋ ከዋናው መሸጫ ጋር ተዳምሮ የውጭ ገንዘቦችን ከባንኮች ለማግኘት የሚጠየቀን ገንዘብ ከጥቁር ገበያው ጋር የተቀራረበ አድርጎት ቆይቷልም ተብሏል።
ይሄ ደግሞ ራሳቸውን ባንኮቹንም የጎዳ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ዶክተር ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡
ብሄራዊ ባንክ ያሳለፈው ሌላኛው ውሳኔ ወደ ውጪ ሀገር የሚሄዱ የግል ተጓዦች እንዲያገኙ የሚፈቀድላቸው የውጭ ምንዛሪ ከአምስት ሺህ ዶላር ወደ አስር ሺህ ዶላር ማደጉን ይመለከታል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር ይሁን መባሉን ተከትሎ እንዲህ አይነት ገደቦችን እያላሉ መሄድ የሚጠበቅ እንደሆነ ዶክተር ቴዎድሮስ ተናግረዋል።
የብሄራዊ ባንክ ሌላው ውሳኔ ሸቀጦችን ከውጭ ለማስገባት ሊከፈል የሚችለው ቅድመ ክፍያ በአስር እጥፍ አድጎ ከአምስት ሺህ ዶላር ወደ ሃምሳ ሺህ ዶላር ከፍ ማለቱን ይጠቅሳል።
ቅድመ ክፍያ ወይም አድቫንስ ፔይመንት አንድ ዕቃ ታዞ ቢመጣ ሰውዬው በርግጥም ይገዛል ወይም ፤ ክፍያውንስ ይፈጽማል የሚለውን ለማረጋገጥ፤ የሚከፈል ገንዘብ ወይም ቀብድ እንደሆነ የተናገሩት የምጣኔ ሃብት ባለሞያው የበለጠ መተማመን ሊፈጥር እንደሚችል አክለዋል።
ግዥ የሚፈጸመው ከፍ ባለ ዋጋ ስለሆነ ግን አሁን በቅድመ ክፍያ ወይም አድቫንስ ፔይመንት ላይ የተደረገው ለውጥ፤ የጎላ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለው እንደማይገምቱ ዶክተር ቴዎድሮስ ተናግረዋል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
Komentarze