top of page

ግንቦት 14 2017 - ኢሰመኮ በህክምና ተቋማት በመካሄድ ላይ ያሉ የስራ ማቆም አድማዎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት እንዳይሆኑ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ጠየቀ

  • sheger1021fm
  • May 22
  • 2 min read

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በህክምና ተቋማት በመካሄድ ላይ ያሉ የስራ ማቆም አድማዎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት እንዳይሆኑ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ጠየቀ፡፡


መንግስት ለችግሩ ግልፅና ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡


ኮሚሽኑ የህክምና ባለሙያዎች እያደረጉት ካለው የስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ባለሙያዎች ስለመኖራቸውም አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡


የአያያዝ ሁኔታቸውንም ክትትል እያደረግሁበት ነው ሲል በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ ተናግሯል፡፡


ባለሙያዎቹ በተወካያቸው በኩል ተመጣጣኝ ደሞዝ እያገኘን አይደለም በሚልና ከጥቅማ ጥቅም ፣ ከሙያ እድገትና የተለያዩ እድሎች ፣ ከምቹ የስራ ቦታ የስራ ቦታ ነፃነት ጋር የተያዙ ጥያቄዎችን ሚያዚያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ለጤና ሚኒስቴር ያቀረቡ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውሷል፡፡


የተጠቀሱትንና ሌሎችም 12 ጥያቄዎች በተሰጠው የ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ ምላሽ ባለማግኘታቸውም ካለፈው ግንቦት 5 ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውንም ተረድቻለሁ ብሏል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፡፡


በዚህም መሰረት አዲስ አበባን ጨምሮ በአጋሮ ፣ በአርባ ምንጭ ፣ በባህር ዳር ፣ በፍቼ በጎባ ፣ በሐዋሳ እና ጅማ ከተሞች መረጃ አሰባስቢያለሁ ብሏል፡፡

ኢሰመኮ ጉዳዩን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር ሀላፊዎች ፣ ከጤና ባለሙያ ተወካዮች እና ጉዳዩ ከሚያገባቸው የመንግስት አካላት ጋር ውይይት አድርጊያለሁ ብሏል፡፡


በተጨማሪም ከፊልና ሙሉ የስራ ማቆም አድማውን ተከትሎ ክትትል ባደረገባቸው የጤና ተቋማት የተለያዩ መስተጓጉሎች ማጋጠማቸውንም አረጋግጫለሁ ሲል ተናግሯል፡፡


በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ዳግማዊ ምኒልክ ሀላፊችን አነጋግሮ አሰባሰብኩት ባለው መረጃም በፅኑ ህሙማን ማዕከል የሚገኙ ታካሚዎችን ጨምሮ በሐኪሞች እጥረት ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንዳልቻሉ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡


በሌላ በኩል ከክልል ከተሞች ረዥም ቀጠሮ ጠብቀው ለህክምና የመጡ ታካሚዎች ለእንግልት የተዳረጉ መሆኑንና በህክምና ባለሙያ እጥረት ምክንያት አንዳንድ የህክምና ተቋማት ባለሙያዎች ለረዥም ፈረቃ እንዲሰሩ ለመመደብ መገደዳቸውን እንዲሁም ኢሰመኮ ተናግሯል፡፡


በሌላ በኩል በማህበራዊ ሚድል ቅስቀሳ አድርገዋል በስራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይም ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰዋል ያላቸውን የሕክምና ባለሙያዎችም ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ማረጋገጡን መግለጫው ጠቅሷል፡፡


በቁጥጥር ስር የዋሉ ባለሙያዎችን አያያዝ ላይም ክትትል እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡


የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በጤናው ዘርፍ የሚደረግ የስራ ማቆም አድማ በማህበረሰቡ ጤና እና በህይወት የመኖር መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን በመጥቀስ ባለሙያዎቹ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ግልፅ እና አሳታፊ በሆነ መንገድ መፍትሄ እንዲሰጥ ሲሉ አሳስበዋል፡፡


የህክምና ባለሙያዎችም የህብረተሰቡ የጤና እና በሕይወት የመኖር መብቶችን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡም ዋና ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡


አያይዘውም ከስራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ አስተዳደራዊ እና ሌሎች ማናቸውም እርምጃዎች ህግንና የሰብአዊ መብት መርሆዎችን የተከተሉ እንዲሆኑ አሳስበዋል ፡፡


ኮሚሽኑ በጉዳዩ ላይም የሚመለከታቸው አካላትን በማነጋገር ችግሩ በውይይት እንዲፈታ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል ብለዋል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page