ግንቦት 14፣2016 - በምስራቅ ወለጋ ባለፉት 2 ዓመታት፤ በአንድ ወረዳ ብቻ 556 መኖሪያ ቤቶች በታጣቂዎች ተቃጥለዋል ተባለ
- sheger1021fm
- May 22, 2024
- 1 min read
በምስራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት 2 ዓመታት፤ በአንድ ወረዳ ብቻ 556 መኖሪያ ቤቶች በታጣቂዎች ተቃጥለዋል ተባለ፡፡
ከተቃጠሉት ውስጥም የሚበዙት የአማራ ተወላጆች የመኖሪያ ቤቶች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን የኦሮሞ ተወላጆች ቤትም ተቃጥለዋል ተብሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዲጋ በተባለ አንድ ወረዳ ብቻ በሁለት ዓመት ዉስጥ 3334 ሰዎችም በፀጥታ ችግር ምክንያት መፈናቀላቸው ተነግሯል፡፡
በወረዳው በአጠቃላይ 765 አባወራዎች መፈናቀላቸውና ከእነዚህ መካከልም 386 አባወራዎች በእዚያው ዲጋ ወረዳ በኮምፕ ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ከ200 የሚበለጡ አባወራዎች ደግሞ ከነቤተሰባቸው ወደ አማራ ክልል እንደሄዱም ተጠቁሟል፡፡
እነዚህ አባወራዎች የተፈናቀሉት፤ መልካ ቤቲ ጂቱ፣ በሬዳ ሶሮማ፣ አርጆ ቆቴቡላ እና ሰባተኛ ካምፕ ተብለው ከሚጠሩ 4 የወረዳው ቀበሌዎች መሆኑንም ሰምተናል፡፡
ይህንን ለሸገር የነገሩት በምስራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ ቡሳ ጎኖፋ(አደጋ ስጋት ስራ አመራር) አስተባባሪ ወንድሙ ምትኩ ናቸው፡፡

በአሁን ወቅት በቦታው አንጻራዊ ሰላም እየታ ነው ያሉን አቶ ወንድሙ፤ ተፈናቃዎቹን ቀስ በቀስ ወደ ቀደመው ቀዬአቸው የመመለስ ስራ ተጀምሯል ብለውናል፡፡
ተፈናቅለው ከነበሩት የኦሮሞ ተወላጆች የሚበልጡት ወደ ቀደሞ ቤታቸው የተመለሱ ቢሆንም 120 አባውራዎች አሁንም ስጋት ስላለ አልተመለሱም ተብሏል፡፡
ቤታቸው ከተቃጠሉባቸው አባወራዎች መካከል ለ97ቱ መንግስት ቤት ሰርቶ እንዲገቡ አድርጓል ሲሉ አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡
እስከ ሰኔ 30 ድረስ የአማራ ተወላጆችንም ጨመሮ አሁን ያልተመለሱት የአሮሞ ተለወላጆችን ለመመለስ እቅድ ይዘን እየሰራን ነው ብለውናል፡፡
ይህ ማለት ግን አካባቢው ሰላም ሳይረጋገጥ ‘’በአንዴ ኑ ተመለሱ ይባላሉ’’ ማለት እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡
እየተመለሱ ያሉ ተፈናቃዮችም ቢሆን ቤት ንብረታቸው ከመውደሙ በተጨማሪ፤ መሬታቸውን ሳያርሱ የቆዩ መሆናቸው ሌላው አሳሳቢ ችግር እንደሚሆንባቸው ተነግሯል፡፡
በዚህም የተነሳ ለተፈናቃዮች ረጂ አካላት የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘጉላቸው፤ የወረዳው መንግስት ጠይቋል፡፡
ሸገር ተፈናቃዮቹ ስላሉበት አጠቃለይ ሁኔታ እና ስለ አካባቢው ወቅታዊ የፅጥታ ሁኔታ የወረዳው አስተዳዳሪ መንግስቱ መገርሳን ጠይቆ ተከታዩን ምላሽ አግኝቷል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን ያሰናዳውን በፍቅሩ አምባቸው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments