እንደ ዝዋይ፣ ሃዋሣ እና አርባ ምንጭ ያሉ አካባቢዎችን የሚያካልለው ‘’የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ’’ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶቹ ይታወቃል።
ለተቀረው የኢትዮጵያ ክፍልም ምርቶቹ ሠፋ ባለ መልኩ ከዚሁ አካባቢ እንደሚቀርቡ ይነገራል።
በአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱ የተሠማሩት አርሶ አደሮች ታዲያ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከለከሉ ፀረ ተባይ መድሃኒቶችን እንደሚጠቀሙ ጥናት አሳይቷል።
ጥናቱን ያደረጉት የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ህይወት(ባዮሎጂ) ትምህርት ክፍል መምህራን እንደነገሩን፤
መድሃኒቶቹ አንዴ ከተረጩ በቀላሉ ከአካባቢ አይጠፉም።
በስፍራው በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ ከተባሉ 33 ፀረ ተባይ መድሃኒቶች 24ቱ ቲማቲም ላይ መገኘታቸውን፤
የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር ዳንኤል ወ/ሚካኤል ነግረውናል።
ፀረ ተባይ መድሃኒቶቹ በዝናብ ውሃ እና በጎርፍ እየታጠቡ ወደ ሃይቆችም ገብተዋል ያሉን ዶክተር ዳንኤል፤
በጥናቱ 20 ፀረ ተባይ መድሃኒቶች በሃዋ ሃይቅ ውስጥ እንዳሉ አረጋግጠናል ብለዋል።
በሃይቁ ወለል ላይ ደግሞ 18 ፀረ ተባይ መድሃኒቶች መገኘታቸውን ነግረውናል።
ፀረ ተባዩ ያለበትን ቲማቲም በተደጋጋሚ የሚመገብ ሰው በጊዜ ሂደት ሁለት አይነት ህመም ሊከሰትበት እንደሚችል በጥናታችን ለይተን ብለዋል መምህሩ።
በሽታ የመከላከል አቅምን የሚቀንሱ እንዲሁም ሆርሞን እና የመዋለድ ስርአትን የሚያዛቡት የመጀመሪያዎቹ አይነት እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
በአካባቢው በቲማቲም ላይ ከተገኙት ፀረ ተባይ መድሃኒቶች ሰባቱ በጊዜ ብዛት ለካንሠር ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ዶክተር ዳንኤል ነግረውናል።
ያ ማለት ግን ሰዎች ቲማቲሙን እንደ ተመገቡ በካንስር ይያያዛሉ ማለት እንዳልሆነ አስገንዘበዋል።
እሳቸውም በአለም አቀፍ ደረጃ ክልከላው ሲደረግ መድሃኒቶቹ ከመጋዘኖች አለመወገዳቸውን በመጥቀስ፤ በኮንትሮባንድም እንደሚገቡ በማከል ምላሽ ሰጥተውናል።
በዋጋቸው ርካሽ፤ ተባይ በማጥፋት አቅማቸው ደግሞ ጠንካራ መሆናቸው ነገሩን አወሳስቦታልም ብለውናል።
ሰዎች ፀረ ተባይ መድሃኒቶች ያሉባቸውን አትክልቶች እንደገዟቸው ከመመገብ አውለው እና አሳድረው ቢጠቀሟቸው የሚል ምክረ ሀሳብ የጥናት ቡድኑ ሰጥቷል።
ስለ መድሃኒቶቹ ጉዳት መረጃ መስጠት እና ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments