top of page

ግንቦት 12፣2016 - በምስራቅ ወለጋ ተፈናቅለው ለሚገኙ ሰዎች እርዳታ እንዲደረግ ተጠየቀ

በምስራቅ ወለጋ ተፈናቅለው ለሚገኙ ሰዎች እርዳታ እንዲደረግ ተጠየቀ፡፡


በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ፤ 2,500 ሰዎች በዲጋ ወረዳ ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል፡፡


የኢትዮጵያ ሲቭል ማህብረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ ጄፕሮ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ለእነዚህ ተፈናቃዮች ድጋፍ አድርጓል፡፡


በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ረጂ ድርጅቶች ወደ ቦታው ገብተው እርዳታ ለማድረስ ፈርተው ቆይተዋል ተብሏል፡፡


በአሁን ሰዓት በአንፃራዊነትም ቢሆን በአካባቢው እርዳታ ለማድረስ አስቻይ ሁኔታ እንዳለ ተነግሯል፡፡


ስለዚህም በብዙ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች፤ ረጂ አካላት እጃቸውን እንዲዘረጉ ተጠይቀዋል፡፡


የሲቨል ማህበረሰብ ድርጀቶች ባለስልጣን በበኩሉ ለተረጂዎች የሚውል 3 ሚሊዮን ብር መድቤለሁ ብሏል፡፡


ከዚህም ብር ውስጥ 1 ሚሊዮኑ ለዲጋ ወረዳ ተፈናቃዮች እርዳታ ውሏል መባሉን ሰምተናል፡፡

በባለስልጣኑ የፈንድ አስተዳደርና ንብረት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ሀ/ማርያም አየለ፤ በአካባቢው እርዳታ የሚሹ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትም ሆኑ ሌሎች ማናቸውም ረጂ አካላት ለተፈናቃዮቹ ትኩተት እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡


እርዳታውን በማስተባበር ያደረሰው የጄፕሮ(Jiret Peace And Reconciliation Organization) ዳይሬክተር ዳዊት ደመቀ፤ በምስራው ወለጋ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ስፍራው ድረስ ሄደን ተመለከተናል ብለዋል፡፡


በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በበዙ ቸግር ውስጥ እልዳሉም ነግረውናል፡፡


ለረጂ አካላትም የአብረን ሰርተን ሰዎቹን እንርዳ ጥሪም አቅርበዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኘው ዲጋ ወረዳ በአንድ መጠለያ ቦታ በ386 አባወራዎች ስር 2500 ሰዎች እንደሚገኙ የወረዳው ቡሳ ጎኖፋ(አደጋ ስጋት ስራ አመራር) ሀላፊ ወንድሙ ምትኩ ለሸገር ነግረዋል፡፡


የዲጋ ወረዳ አስተዳዳሪ መንግስቱ መገርሳ በበኩላቸው፤ ተፈናቃዮቹ አሁን ላይ ምግብ እያገኙ ያሉት ከአካባቢው ህብረተሰ እና ከመንግስት በሚሰበሰበው ድጋፍ ነው ብለውናል፡፡


እየተደረገ ያለው ድጋፍ ግን በቂ ባለመሆኑ የሚረዱ አካላትን እርዳታ ጠይቀዋል፡፡


እንደ ስጋት በተለያዩ አካላት ለሚነሳው የጸጥታ ችግርም ‘’ሀላፊነቱ እኛ እንወስዳልን’’ ብለዋል፡፡


ከተፈናቃዮቹ የሚበዙት የአማራ ተወላጆች እንደሆኑ እና ወደ ነበሩበት ቀዬ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከወረዳው አስተዳዳሪ ለማወቅ ችለናል፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw


Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio


Website: https://www.shegerfm.com/


Comments


bottom of page