ግንቦት 1 2017 - የልብ ህክምና ሆስፒታል በማቋቋም የሚታወቁት የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ በስዊድን ሀገር ተፈፀመ
- sheger1021fm
- May 9
- 1 min read
በኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ የልብ ጠጋኞች አንዱ የሆኑትና የመጀመሪያውን የልብ ህክምና ሆስፒታል በማቋቋም የሚታወቁት የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ በስዊድን ሀገር ተፈፀመ፡፡
የአዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል እና ታዝማ የውስጥ ደዌና የሰርጂካል ማዕከል መስራቹ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ባለፈው ቅዳሜ በስዊድን ሀገር ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ፍቅሩ በኢትዮጵያ የልብ ህክምና እና በቂ ባለሙያ ባልነበረበት ጊዜ በስዊድን ሀገር የልብ ህክምናን ስፔሻላይዝድ አድርገው ቀድመው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ዘመናዊውን ህክምና ከጀመሩት ከቀዳሚዎቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ ፍቅረማርያም በሙያቸው የልብ ህክምናና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ናቸው፡፡
በአዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ሆነው ይሰራሉ፡፡
እሳቸው እንደነገሩን የልብ ቀዶ ህክምና ዛሬ በኢትዮጵያ በግልም በመንግስት ተቋማት ተስፋፍቷል፡፡
ከባድና ውስብስብ የሚባሉ የህክምና ዓይነቶንም በሀገር ውስጥ መስራት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
ከዚህ እድገት ጀርባ የዶ/ር ፍቅሩ አስተዋጽኦ ትልቅ ነው ይላሉ፡፡

ከግሉ ባለፈ በመንግስት ሆስፒታልም ህክምናው ዛሬ የደረሰበት እንዲደርስ ዶ/ር ፍቅሩ ብዙ አግዘዋል ብለዋል፡፡
የጥቁር አንበሳው የልብ ህሙማን ህክምና ማዕከል ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲና ሌሎቹም የልብ ህክምናን እንዲጀምሩ ካገዙት ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ሲዊድናዊ የሆኑት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ካለፈው አንድ አመት ወዲህ የጤናቸው ነገር ታውኮ በህክምና ላይ እንደነበሩ የነገሩን ዶ/ር ቴዎድሮስ ከህልፊታቸው ከሳምንት በፊትም በአዲስ አበባ ተገኝተው የአዲስ የልብ ህክምና የማስፋፊያ ስራን መርቀው መመለሳቸውን ነግረውናል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ህይወታቸውን ያለፈው የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የቀብራቸው ስነ ስርዓት ዛሬ በስዊድን ስቶኮልም ተፈፅሟል፡፡
በተወለዱ በ74 አመታቸው ህይወታቸው ባለፈው ቅዳሜ ያለፈው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
ሸገር ለቤተሰቦቻቸው ለሙያ አጋሮቻቸው እና ወዳጆቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
Yorumlar