top of page

ግንቦት 1 2017 - ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 270 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናገረ

  • sheger1021fm
  • May 9
  • 2 min read

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ያገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 270 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናገረ።


ኩባንያው ባለፈው ዓመት 2.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውሶ በማርች 31 ቀን 2025 (እ.ኤ.አ) በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የ270 በመቶ እድገት በማስመዝገብ 7.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል ሲል ለሸገር በላከው መግለጫ ጠቅሷል።


ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አሁንም በኢንቨስትመንት ደረጃ ላይ መሆኑን ተናግሮ በዚህ በጀት ዓመት ለሥራ ማስኬጃ ያወጣው ወጪ ካስገባው ገቢ በ47 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ነው ብሏል።


ይህም በዚህ የኩባንያው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወቅት የሚጠበቅ ነው ያለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ ቢመጣም ባለፉት ወራት የነበረው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ተጽዕኖ ያረፈበት ነው ብሏል።

ኩባንያው በመግለጫው የ4G አገልግሎቶችን በ3,141 ቦታዎች ላይ በተተከሉ የኔትወርክ ማማዎች አማካኝነት 50% የኢትዮጵያን ክፍል አዳርሻለሁ ብሏል።


ይህም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በአጠቃላይ 8.8 ሚሊዮን የ90 ቀን ንቁ የድምጽ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ደንበኞች ለማፍራት እና ጥራት ለማስተናገድ አስችሎኛል ሲልም አስረድቷል።


ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የ103 ከመቶ ጭማሪ ሲሆን፤ 7.1 ሚሊዮን የ90 ቀናት ንቁ የኢንተኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቻችን የዳታ አጠቃቀምም በወር በአማካይ 6.5GB ሲሆን፣ ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ተጠቃሚ ፍጆታ 53 ከመቶ ጭማሪን አስመዝግቧል ሲል ጠቅሷል።


የM-PESA ደንበኞች 2.4 ሚሊዮን መድረሳቸውን ያስረዳ ሲሆን በዚህም 15.8 ቢሊዮን በዲጂታል መላ ብር መዘዋወሩን ተነግሯል።


እንደ ነዳጅ ክፍያን መፈጸም፣ ከውጭ ሀገራት የሚላክ ገንዘብን ማስተላለፍ እንዲሁም ከባንክ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር የአየር ሰዓት ግዢ እና የአገልግሎት ክፍያዎችን መፈጸም ማስቻል ስራዎች ለስኬቱ እንደማሳያ ተነስተዋል።


ከቴሌኮም እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች በተጨማሪም በትምህርት፣ ጤና እና ግብርና ፕሮጀክቶች ለማህበረሰብ አገልግሎቶች 100 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ፤ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላፕቶፖችን እና ራውተሮችን ከ6 ወራት ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት አበርክቻለሁ ሲልም ተናግሯል።


በተጨማሪም በጅግጅጋ የአሸዋ ገበያ በደረሰ የእሳት አደጋ ሙሉ በሙሉ የወደመውን የገበያ ማዕከል መልሶ በመገንባት፣ በጎፋ የመሬት መንሸራተት እና በአፋር የመሬት መንቀጥቀጥ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ምግብ እና ጥሬ እቃ በማቀረብ፤ እንዲሁም ለመቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ማስፋፊያ ሥራ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፎችን በበጀት ዓመቱ አድርጌያለሁ ብሏል።


የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄሌፑት “ባለፉት 12 ወራት በጠንካራ ኢንቨስትመንት እና ስልታዊ አመራር የደንበኞቻችንን ብዛት አሳድገናል፣ የኔትወርክ ሽፋናችንን እና አገልግሎታችንን በመላው ኢትዮጵያ አስፋፍተናል ሲሉ መናገራቸውን ከመግለጫው ላይ ተመልክተናል።


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page