በሱዳን ያለውን ጦርነት ሸሽተው በኢትዮጵያ ሰሜን ጎንደር ዞን አውላላ መጠለያ ጣቢያ ከነበሩ ስደተኞች ውስጥ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉት መጠለያ ጣቢያውን ለቀው መውጣታቸው ተሰማ፡፡
እነዚህ ከመጠለያ ጣቢያ የወጡት የሱዳን ስደተኞች በመተማ ጎንደር አውራ ጎዳና ላይ ይገኛሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን ለሸገር ተናግሯል፡፡
ከሰሞኑ በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መጠለያቸው ጥለው ወጥተዋል የሚሉ ዘገባዎች ወጥተው ነበር፡፡
ሸገር በጉዳዩ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR)ን ጠይቋል፡፡
ድርጅቱ ለሸገር በኢ-ሜይል በላከው መልስ ባለሳለፍነው ሳምንት ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም በአብዛኛው ከሱዳን የመጡ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች በሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኘው አውላላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መውጣታቸውን አረጋግጧል፡፡
ስደተኞች ከመጠለያ ቦታው በ1.5 ኪ.ሜትር ርቀት በመተማ ጎንደር መንገድ ላይ እንደሚገኙም ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡
ስርቆት፣ የተደራጀ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ ጠለፋ የመሳሰሉ ወንጀሎች ተፈናቃዮቹን መጠለያ ጣቢያዎቻቸውን ጥለው እንደወጡ እንዳስገደዷቸው ተፈናቃዮች ነግረውኛል ብሎ ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡
የሚቀርብላቸው አገልግሎት አለመሻሻልም መጠለያውን ጥለው እንዲወጡ እንዳስገተደዳቸው ተናግረዋል ተብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ሀላፊዎች ጋር በመሆን ተፈናቃዮቹ ጥለውት ወደመጡበት መጠለያ እንዲመለሱ ጥረት ቢያደርግም የተወሰኑት ብቻ ሚያዚያ 25/2016 መመለስ ችለዋል ብሏል፡፡
ኩመራ በአማራ ክልል የሚገኝ ሌላኛው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሲሆን ከዚህም ጣቢያ ከ300 - 400 የሚሆኑት ስደተኞች ወጥተው በፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ ጎዳና ላይ ይገኛሉ ሲል ኮሚሽኑ ለሸገር ተናግሯል፡፡
ኮሚሽኑም የእነዚህም ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በሱዳን ያለውን ጦርነት ሸሽተው 53,500 ስደተኞች በመተማ እና ኩምሩክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ባሉ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments