የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እየተደረጉ ያሉ ግጭቶች ቆመው ሁሉም አካላት ወደ ንግግር አንዲመጡ ጠየቀ፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በበኩሉ ታጠቂዎች በምክክሩ እንዲሳተፉ ከለላ እንዲደረግላቸው መንግስትን የመጠየቅ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ በሃገራዊ ምክክሩ ሁሉም አካላት ካልተሳተፉ ምክክሩ ውጤት ላያመጣ ይችላል ብለዋል፡፡
በጫካ ያሉ ታጣቂዎችም በምክክሩ አንዲሳተፉ ለዚህም ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ምክር ቤቱ የጠየቀ ሲሆን ይህ ካልሆነ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ውጤት ላያመጣ ይችላል ሲል የጋራ ምክር ቤቱ ስጋቱን ለሸገር ነግሯል፡፡
ምክር ቤቱ ሌላው ስጋት ብሎ ያነሳው ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አዋጅ ግጭቶችን የማስቆም ሃላፊነት አልተሰጠውም ግጭት ሳይቆም በግጭት ውስጥ የሚደረግ ምክክር ደግሞ ውጤት ላያመጣ ይችላል ብሏል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከጅምሩ ጀምሮ በምክክሩ አለሳተፍም ያሉ የፖለቲካ ፓረቲዎች ፣በተለያየ ክልሎች ያሉ ታጣቂዎች በምክክሩ እንዲሳተፉ እንዲደርግ ኮሚሽኑን ጠይቋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ምክክሩ አሳታፊ እንዲሆን ሁሉም አካላት እንዲሳተፉ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ያኮረፉ እና ጫካ የገቡ ታጣቂዎችም በምክከሩ እንዲሳተፉ ከሲቪል ማህበረስብ እና ከተለያዩ አለም ሀገራት ኤምባሲዎች ጋር እየሰራን ነው ሲሉ ለሸገር ነግረዋል፡፡ጫካ የገቡ አካላት እንዲሳተፉ በመገናኛ ብዙሃን ተደጋጋሚ ጥሪዎችን እያደረግን ነው ያሉት ኮሚሽነር ዮናስ ሕጋዊ የሆነ መስሪያ ቤት ስለሌላቸው ጥሪ ለማድረግ ተቸግረናል፣ እዚህ ነን አለን የሚሉ ከሆነ የተመካከሩ ጥሪ ወረቀት ይዘን ለመሄድ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
Comments