የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡን ሰላም ከሚያውኩ ቅስቀሳዎች እንዲርቁ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።
- May 21
- 1 min read
ግንቦት 13/2018
የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡን ሰላም ከሚያውኩ ቅስቀሳዎች እንዲርቁ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።
ከ10 ቀናት በኋላ የሚካሄደው ሃገር አቀፍ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ሃገራዊ ሰላምን ለማፅናት በሚል የፊታችን እሁድ የአደባባይ የፀሎት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተናግሯል።
የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች በወሰኑት መሰረት የፊታችን እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው አራዳ ፓርክ ሃገር አቀፍ የፀሎት መርሃ ግብር መሰናዳቱን የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በጉዳዩ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።

ቀሲስ ታጋይ የፀሎት መርሃ ግብሩን አላማዎች ሲጠቅሱም በሃገር ውስጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለማገዝ ምዕመናን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ የፓለቲካ ፓርቲዎችም የህዝቡን ሰላም ከሚያውኩ ቅስቀሳዎች እንዲርቁ ለመጠየቅ፤ እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና ሰላምን ለማምጣት የፈጣሪ እገዛን ለመጠየቅ የሚደረግ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በመገናኛ ብዙሃን አጭር የሰላም መልዕክቶች ይተላለፋሉ፤ ከነገ ጀምሮ ደግሞ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በእጅ ስልኮች ተመሳሳይ መልዕክቶች ይተላለፋሉ፤ እሁድ በሚኖረው የአደባባይ ፀሎት ከሁሉም ቤተ እምነት የተወጣጡ ከ1000 በላይ ሰዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በመርሃ-ግብሩ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የምርጫ ቦርድና የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ይገኛሉ፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው በክልሎች ባለው መዋቅር በተመሳሳይ ሰዓት በሁሉም ክልሎች የአደባባይ ፀሎቱ ይካሄዳል መባሉን ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments