top of page

የፌድራል መንግስት በመንፈቅ ዓመቱ 93.3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት እንደገጠመው የገንዘብ ሚኒስቴር ያውጣው የግማሽ ዓመት ሪፖርት አሳየ፡፡

  • Apr 30
  • 2 min read

ሚያዝያ 22/2018


የፌድራል መንግስት በመንፈቅ ዓመቱ 93.3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት እንደገጠመው የገንዘብ ሚኒስቴር ያውጣው የግማሽ ዓመት ሪፖርት አሳየ፡፡


በሌላ በኩል የዘንድሮ የንግድ ሚዛን ልዩነት 6.2 ቢሊዮን ዶላር መሆኑም ተጠቅሷል፡፡


የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው ዘርዘር ያለና የበጀት አጠቃቀምን በሚያሳየው ሪፖርቱ ባለፉት 6 ወራት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የተሰበሰበው ገቢ እንዲሁም አጋር ከተባሉ አካላት የተገኘውን ጨምሮ አጠቃላይ ገቢው 704.7 ቢሊዮን ብር መሆኑን ይጠቅሳል፡፡


ይሁንና በዚሁ ጊዜ ለመደበኛ፣ ለካፒታል ወጪዎችና ለክልሎች የተሰጠው የበጀት ድጎማ ተዳምሮ ወጪውን 798.2 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡


በዚህም ወጪውና ገቢው ባለመመጣጠኑ የ93.3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት እንደገጠመ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡


የገጠመው የበጀት ጉድለት ከሃገር ውስጥና ከውጭ በተገኘ የፋይናንስ አቅርቦት በመሸፈኑ ጉድለቱ ተስተካክሏል ተብሏል፡፡


ለ2018 የበጀት ዓመት ለፌድራል መንግስቱ የፀደቀው በጀት 1.9 ትሪሊዮን ብር መሆኑን ያስታወሰው የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት በዚህ 6 ወር የተሰበሰበው የ704.7 ቢሊዮን ብር ገቢ በዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 48.1 በመቶ ያህሉን ይሸፍናል፣ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር የ55.4 በመቶ ብልጫ አለው ብሏል፡፡


ከአጠቃላይ ገቢው ከታክስ የተሰበሰበው 579.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን በዓመቱ ከታክስ ለመሰብሰብ በእቅድ ከተያዘው ገቢ 52 በመቶውን እንደሚሸፍንና ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከርም የ62.7 በመቶ የዘንድሮው ብልጫ እንዳለው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ታክስ ካልሆኑ የተለያዩ ገቢዎች የተሰበሰበው 57.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን ከዓመታዊ እቅዱ 44 በመቶውን ይሸፍናል፡፡


በተጨማሪም የፌድራሉ መንግስት ለፕሮጀክቶች የሚውል 235.5 ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች ማግኘቱንም


በተሰራው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ኢትዮጵያ ተከታታይነት ያለው እንደገት ማስመዝገቧን የሚናገረው ይኸው የመንግስት ሪፖርት በግማሽ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ጥቅል ምርት(ጂዲፒ) በ9.2 በመቶ ማደጉን አስፍሯል፡፡


ለጂዲፒው ማደግ አስተዋፅኦ በማድረግ የቀዳሚነት ስፍራውን የሚይዙት ደግሞ የግብርና፣የማዕድን፣የኮንስትራክስንና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ናቸው፡፡


እስካሁን የተሰሩ ስራዎች እና የመጡት ውጤቶችን መሰረት በማድረግ በዓመቱ መጨረሻ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት 10.2 በመቶ እንደሆነም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡


በሪፖርቱ ሌላው የተጠቀሰው የሃገሪቱ የወጪ ገቢ ንግድን የተመለከተው ጉዳይ ነው፡፡


በዚህም ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት ከፍተኛ ነው የተባለውን የ5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከወጪ ንግድ ማግኘቷንና የዓምናው የ2017ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት የዚህ ዘርፍ ገቢ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሷል፡፡


የዘንድሮ የወጪ ንግድ ገቢ ከፍ ለማለቱ ምክንያት ናቸው ተብለው የተጠቀሱት የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ላይ ማስተካከያ መደረጉ፣የወጪ ንግዱን ኢ-መደበኛ ከነበረበት በስርዓት የሚመራ ማድረግ መቻሉና ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ሸቀጦች አለም ላይ ያላቸው ዋጋ በመጨመሩ እንደሆነ ነው፡፡


በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በመንፈቅ ዓመቱ 11.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦችን ከውጭ አስገብታለች፡፡


በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ሸቀጦችን ከዓለም ገበያ ለመግዛት ባወጣችው 11.2 ቢሊዮን ብር እና ሸቀጦችን ወደ ውጭ በመላክ ባገኘችው የ5 ቢሊዮን ዶላር መካከል ከእጥፍ በላይ ልዩነት ታይቷል፡፡


ማለትም የዘንድሮ የንግድ ሚዛን ልዩነት የ6.2 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የሚጠቅሰው የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር የዘንድሮው የንግድ ሚዛን ልዩነት ከመቀነስ ይልቅ ጨምሯል፡፡


የፌድራሉ መንግስት ከአለም አቀፍ የልማት አጋሮች በበጀት ዓመቱ 235.ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ አቅዶ ነበረሲሆን በ6 ወራት ውስት የተገኘው ግን 67.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ይህም ከዓመታዊ እቅዱ 28.8 በመቶ እንደሆነ ከሪፓርቱ ተመልክተናል፡፡


ቀሪው በሁለተኛው የበጀት ዓመት ወቅት ይገኛል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page