በኬንያ ሲካሄድ የሰነበተው የአፍሪካ የአየር ለውጥ ጉባኤ ተካፋዮች ለችግሩ ማቃለያ የገንዘብ ድጋፍ የሚገኝበትን ምክረ ሀሳብ አቀረቡ፡፡
መግለጫም ማውጣታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡
በተለይም ለችግሩ ማቃለያ ለድሆቹ እና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገሮች የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግበት መላ እንዲመታ በመግለጫው ተጠይቋል፡፡
ከነዚህም መካከል የእዳ እፎይታ እና ስረዛ እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
ቀደም ሲል የበለፀጉት ሀገሮች 100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም እምብዛም ስራ ላይ እንዳልዋለ ይነገራል፡፡
በጉባኤው አካባቢ የነበሩ የአየር ንብረት ተሟጋቾች ብዙ ተግባር ትንሽ ወሬ ሲሉ አቋማቸውን ማስተጋባታቸው ተሰምቷል፡፡
የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዘዳንት ኤድጋር ሉንጉ ባለቤት ኢስተር ሉንጉ በምዝበራ ምክንያት ተይዘው መታሰራቸው ተሰማ፡፡
ከቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ጋር የስርቆት ግብረ አበሮቻቸው ነበሩ የተባሉ ሌሎች 3 ሰዎችም ተይዘው መታሰራቸውን ሉሳካ ታይምስ ፅፏል፡፡
ኢስተር ሉንጉ እና ሌሎች 3 ሰዎች የሌላ ሰው የሆነ ንብረት እና ቦታ ቀምተዋል ተብለው እንደሆነ የፖሊስ ሹሞች ተናግረዋል፡፡
የወንጀል ፍሬ የሆነ ሐብት እና ንብረት አከማችተዋል ተብለው መወንጀላቸው ታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ኤድጋ ሉንጉን ጨምሮ በበርካታ የቀድሞ ሹሞች ላይ የምዝበራ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የናይጀርያ የምርጫ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ቦላ ቲኑቡ አሸንፈውበታል የተባለው የምርጫ ውጤት እንዲሰረዝ የቀረበለትን አቤቱታ ውድቅ አደረገው፡፡
ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያደረገው የሌበር የፖለቲካ ማህበር ፕሬዘዳንታዊ እጩ ፒተር ኦቢ እና የፖለቲካ ማህበራቸው ያቀረቡትን አቤቱታ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በአቤቱታው የተነሳውን መሟገቻ አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የምርጫው ውጤት አወዛጋቢ የነበረ ቢሆንም ቦላ ቲኑቡ ባለፈው ግንቦት ወር ቃለ መሐላ በመፈፀም ፕሬዘዳንታዊ ሀላፊነታቸው እንደተረከቡ ዘገባው አስታውሷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሌላኛው እጩ አቲኩ አቡበከር በቀረበውም አቤቱታ ላይ ብይን ይሰጥበታል ተብሏል፡፡
አሜሪካ RSF በተሰኘው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መሪዎች ላይ ማዕቀብ መጣሏን እወቁልኝ አለች፡፡
ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ከሱዳን መንግስት ጦር ጋር ውጊያ ከገጠመ 5 ወራት ሊሆነው ነው፡፡
የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ አዛዥ የሌተና ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወንድም አብዱራሂም ዳጋሎ እና ሌሎች የፈጥኖ ደራሹ ሀይል የጦር መሪዎች ማዕቀቡ እንደሚመለከታቸው TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡
በ RSF የጦር መሳሪያዎች ላይ ማዕቀብ የተጣለባቸው በተለይም በዳርፉር ግዛት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ነው፡፡
ማዕቀቡ የጉዞ እና የገንዘብ ማንቀሳቀስ እገዳን እንደሚጨምር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሹሞች ተናግረዋል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comentários