‘’አክሱም ከተማ ወደ ሰላሟ ብትመለስም እንደቀድሞው ጎብኚዎች እየመጡ አይደለም’’ ሲል የአክሱም ከተማ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ተናገረ፡፡
‘’ከተማው ውስጥ አሁን ሙሉ ለሙሉ ሰላም ሰፍኗል’’ የሚለው ማህበሩ እየመጡ ያሉ ጎብኚዎች ቁጥር ግን አነስተኛ ነው ብሏል፡፡
የአክሱም ከተማ የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ጎይቶም ትዕዛዙ ‘’ከሰሜኑ ጦርነት በፊት #አክሱም ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት ፍሰት የነበረባት ስፍራ ነበረች’’ ብለዋል፡፡
‘’በጦርነቱ ምክንያት የቱሪስቶች ፍሰቱ ቆሞ ነበር የተባለ ሲሆን አሁን ባለው የሰላም ሁኔታ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ወደ አክሱም እያቀኑ ቢሆንም ቁጥራቸው ግን እጅ አነስተኛ ነው’’ ሲሉ ነግረውናል፡፡
#የቱሪዝም ባለሞያውና የሰለብሪቲ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ካሣ ወደ አክሱም ጥናት ለማድረግ መጓዛቸው ነግረውናል፡፡
‘’አሁን ላይ አክሱም ሙሉ ለሙሉ ሰላም ሆናለች’’ የሚሉት አቶ አሸናፊ ከተማው ‘’ለቱሪስቶች እራሷን ዝግጁ አድርጋለች እየጠበቀች ነው ጎብኚዎች ወደ አክሱም ሊሄዱ ይገባል’’ ብለዋል፡፡
አቶ አሸናፊ ‘’አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እራሳቸውን በሚገባ እያዘጋጁ መሆኑን ታዝቤያለሁ’’ ያሉ ሲሆን ‘’ነገር ግን ግብአት አቅርቦት ላይ እጥረት አለ በተለይም እንደ ሱፐርማርኬት ያሉ ተቋማት ላይ እጥረት ይታያል በዚህ ዙሪያ ሊሰራ ይገባል’’ በማለት አሳስበዋል፡፡
የአክሱም ከተማ የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ጎይቶም ትእዛዙ በበኩላቸው ከጦርነቱ በኋላ ሆቴሎች ወደ ስራ ለመግባት የቻሉትን ያህል ዝግጅት እያደረጉ ቢሆንም የተማረ የሰው ሃይል እጥረት ግን እየገጠማቸው ነው በማለት ነግረውናል፡፡
መንግስትም ሆነ ባለድርሻ አካላት ይህንን ቢያደርጉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የበለጠ ጠንክረው ይሰራሉ ሲሉ ፕሬዘዳንቱ አሳሰበዋል፡፡
በረከት አካሉ
Comments