የማዕከላዊ እስያዋ ሀገር ኪርጊስታን መንግስት አሜሪካን በውስጥ ጉዳዬ ምን ጥልቅ አደረገሽ ማለቱ ተሰማ፡፡
ሁለቱን አገሮች አላግባባ ያለው ጉዳይ በአገሪቱ ከውጭ አገር ተቋማት ጋር ግንኙነት ያላቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚመሩ እና የሚተዳደሩበት ህግ መረቀቁ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ረቂቁ በእጅጉ አሳስቦናል የሚል ደብዳቤ መፃፋቸው ታውቋል፡፡
የኪርጊስታን መንግስት በበኩሉ ለአሜሪካ ደርሶ በውስጥ ጉዳያችን ምን ጥልቅ አደረገሽ የሚል ምላሽ መስጠቱ ተሰምቷል፡፡
ጉዳዩ የራሳችን ጉዳይ በመሆኑ ጣልቃ አትግቡብን ማለቱ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሣ የፍልስጤማውያንን የነፃነት ትግል መደገፋችንን እንቀጥላለን አሉ፡፡
ራማፎሣ መንግስታችን ከሕዝቡም አብዛኛው እንዲሁም ፣ ገዢው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ የፖለቲካ ማህበር /ANC/ የፍልስጤም ሕዝብ የነፃነት ትግል ደጋፊዎች ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ዘመቻዋ በሰላማዊ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈፀመች ነው ስትል በአለም ፍርድ ቤት መክሰሷ ይታወቃል፡፡
ራማፎሣ ፍልስጤማውያን የነፃ አገር ባለቤቶች እንዲሆኑ ምንግዜም ከጎናቸው እንቆማለን ብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግታት ፍልስጤማውያን ነፃ እስካልወጡ ድረስ እኛ ተነጥለን ነፃነት አይሰማንም የሚል አቋም እንዳለው ዘገባው አስታውሷል፡፡
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ጫፍ በምትገኘው ራፋህ ዘመቻ እንዳትከፍት ግብፅ መጠየቋ ተሰማ፡፡
ግብፅ የእስራኤል የራፋህ ዘመቻ ከሚነገረውም በላይ ሰብአዊ ቀውስ አስከታይ ነው ማለቷን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
የእስራኤል የራፋህ ዘመቻ ከግብፅ ብቻ ሳይሆን ከብዙ ወገኖች በኩል ተቃውሞ እየቀረበበት ነው፡፡
ሰግተናል ባዮችም በርክተዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም እስራኤል የራፋህ ዘመቻዋን እንድትተወው እየጎተጎቱ ነው፡፡
የእስራኤል ጦር ግን በራፋህ የአየር ድብደባ መጀመሩ እየተሰማ ነው፡፡
ራፋህ በግብፅ ወሰን ላይ የምትገኝ የፍልስጤማውያን ከተማ ነች፡፡
በስፔን የአደገኛ ዕፅ ማጓጓዣ ጀልባን ለመያዝ በተፈጠረ ማሳደድ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 8 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡
በተኩስ ልውውጡ ከተገደሉት መካከል ሁለቱ የፖሊስ መኮንኖች እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በተኩስ ልውውጡ ከተገደሉት ሌላ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች ደግሞ አካላዊ ጉዳት አጋጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
አጋጣሚው የተፈጠረው በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል መሆኑ ታውቋል፡፡
በማሳደዱ 8 የአደገኛ ዕፅ አስተላላፊዎች ተይዘው መታሰራቸው ተጠቅሷል፡፡
የስፔን ደቡባዊ የባህር ዳርቻ የአደገኛ ዕፅ ማስተላለፍ ተግባር የሚቀለጣጥፍበት እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments