top of page

የካቲት 8 2017 - የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስት ጋር የማደርገውን ጥረት ምርጫ ቦርድ እያዳናቀፈብኝ ነው ሲል ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ከሰሰ

የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስት ጋር የማደርገውን ጥረት ምርጫ ቦርድ እያዳናቀፈብኝ ነው ሲል ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ከሰሰ፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሃት ባዘዝኩት መሰረት #ጠቅላላ ጉባኤ ባለማድረጉና ሌሎችም መከወን ያለበትን ተግባራት ባለመፈፀሙ ለመጭዎቹ 3 ወራት ምንም ዓይነት የፓርቲ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ አግጃለሁ ማለቱን ተከትሎ ፓርቲው በሰጠው ምላሽ ነው ቦርዱን የወቀሰው፡፡

ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ህወሃት እንደ አዲስ መመዝገቡን ጠቅሶ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድና አመራሮችን መምረጥ እንዲሁም መተዳደሪያ ደንቡን ጨምሮ የተለያዩ ሰነዶችን ማፅደቅ ነበረበት ብሏል፡፡


ይህን ባለማድረጉ ለ3 ወራት እግድ እንደተጣለበትና በዚሁ ጊዜ ውስጥም የቦርዱን ትዕዛዝ በማክበር ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ለመከወን ለ #ቦርዱ በደብዳቤ ሲያሳውቅና ቦርዱም ይህን ሲያረጋግጥ እግዱን እንደሚያነሳም አሳውቋል፡፡


ይህ ካልሆነ ግን ህወሃትን ከፖለቲካ ፓርቲነት እንዲሰርዘው ከትናንት በስቲያ በመግለጫው ማስጠንቀቁ ይታወቃል፡፡


ይህን የምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ትናንት ህወሃት ባወጣው መግለጫም #ህወሃት እንደ ቀድሞ አቋሙ እንዲቀጥል እንጂ እንደ አዲስ ፓርቲ ለመመዝገብ ለምርጫ ቦርድ ያቀረብኩት ጥያቄ የለም ብሏል፡፡


ፓርቲው የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆን ከፌዴራል መንግስት ጋር እየሰራ ያለበትን ሂደት ምርጫ ቦርድ ጣልቃ በመግባት እያደናፈቀፈብኝ ነው ብሏል፡፡

ይህም ህጋዊ እንዳልሆነ እና ለሃገርና ለህዝብም የማይጠቅም መሆኑ መታወቅ አለበትም ሲል በመግለጫው ተናግሯል፡፡


የሰላም ስምምነቱ ለመጨረሻ ጊዜ ተፈፃሚ ሆኖ ጉዳዩ እንዲዘጋም ጠይቋል፡፡


#የትግራይ_ህዝብ ፍላጎት ሰላምና ፍትህ ነው ሲል ገልጾ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ትግራይ ውስጥ እንዲኖርም ለማስቻልም መንግስት የሚስፈልገውን ስራ እንዲሰራ ጥሪ አቀርባለሁ ብሏል፡፡


ሕወሃት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አሸባሪ ተብሎ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መፈረጁን ተከትሎ ከፓርቲነት ተሰርዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡


ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ከሽብርተኝት ዝርዝር ቢፋቅም መልሶ ፓርቲ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችል የህግ ማእቀፍ የለም በሚል የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ተሻሽሎ ህወሃት እንደ አዲስ ይመዝገብ ዘንድ በህጉ ተፈቅዷል መባሉም ይታወሳል፡፡


ህወሃት በበኩሉ እንደ አዲስ አልተመዘገብኩም ባይ ነው፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን

Комментарии


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page