የካቲት 8 2017 - በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አጥር የሌላቸው የማረሚያ ተቋማት መኖራቸው ተሰማ፡፡
- sheger1021fm
- Feb 15
- 1 min read
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አጥር የሌላቸው የማረሚያ ተቋማት መኖራቸው ተሰማ፡፡
በዚህም ታራሚዎች ወጥተው የሚጠፉበት ዕድል መኖሩን የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በግንባታ ላይ 10 እና ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ 4 #ማረሚያ_ቤቶች እስካሁንም አለመጠናቀቃቸው ተጠቅሷል፡፡
በክልሉ ለሚገኙ ታራሚዎች ምህረት በሚደረግበት ወቅትም፣ በሀሰተኛ ማስረጃ የሚወጡ ታራሚዎች በርካታ ናቸው ተብሏል፡፡
በዚህም በምህረት መለቀቅ የሚገባቸው እያሉ የማይገባቸው ታራሚዎች ይቅርታና ምህረት እያገኙ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው የክልሉ አካባቢዎች #የሰው_ህይወት እያለፈ መሆኑን ክልሉ የምክርቤት አባላት ተናግረዋል፡፡ ከነዚህ አካባቢዎች ወስጥ የኮሬ ዞን ተጠቅሷል፡፡
ይህ የተነገረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እያካሄደ ባለበት ወቅት ነው፡፡
ትናንት በተጀመረው የክልሉ ጉባኤ በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ሪፖርቶች እና ጥያቀዎች ቀርበዋል፡፡
ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል በኮንሶ ዞን ተወካይ በኩል የቀረበ በ2008 ዓ.ም ያልተከፈለ #የሰራተኞች_ደመወዝ ጉዳይም ይገኝበታል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተከናወኑ ስራዎች ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በዚህም 32.5 ኩንታል ካናቢስ፣ 15 ኪሎ ግራም ጋንጃ እና 254 የሺሻ ዕቃዎች ተይዘዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዞ 58 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው እየተመረመረ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
326 ህፃናት እና 191 አዋቂ ሰዎች በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ እንደተገኙም ተናግረዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 280ዎቹ ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እና በ36 አዘዋዋሪዎች ላይ ደግሞ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡
ትናንት የተጀመረው ጉባኤው ዛሬም የቀጠለ ሲሆን በተነሱ ጉዳዮች ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments