top of page

የካቲት 8፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬይን የምትገኘውን የአቭዲፍካ ከተማን በእጁ ሳያስገባት አልቀረም ተባለ፡፡


ከተማዋ ለበርካታ ወራት ከባድ መስዋዕትነት ጠያቂ ውጊያ ሲካሄድበት እንደነበር ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የአሜሪካው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ አቭዲፍካ በሩሲያ ጦር መያዟ አይቀሬ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


የዩክሬይን ጦር የገጠመው የጦር መሳሪያ እና የተተኳሾች እጥረት ከተማዋን ጥሎ ለመውጣት እንደሚያስገድደው አንስተዋል ኪርቢ፡፡


የሩሲያ ጦር አቭዲፍካን መቆጣጠሩ እርግጥ ከሆነ በአቅራቢያው ያለችውን እና በእጁ የምትገኘውን የዳኔስክን ከተማ ከጥቃት ለመጠበቅ ታላቅ ድርሻ የሚኖረው ነው ተብሏል፡፡




የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) ዩክሬይንን ድሮን በድሮን ሊያደርጋት ነው፡፡


የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ አባል አገሮች ለዩክሬይን 1 ሚሊዮን ሰው አባል በረራ አካላት (ድሮኖችን) እንደሚሰጧት ዋና ፀሐፊው ጄንስ ስቶልትንበርግ መናገራቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ስቶልትንበርግ ከቀድሞው በፈጠነ የድሮን ምርታችንን እንጨምራለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

የዩክሬይኑ ጦርነት ወደ 2ኛ አመቱ ተቃርቧል፡፡


እስካሁን የኔቶ አባል አገሮች ለዩክሬይን የ100 ቢሊዮን ዶላር የጦር ድጋፍ ማድረጋቸውን ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል፡፡

የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ 4 አባል አገሮች ለዩክሬይን አሜሪካ ስሪቶቹን F-16 የጦር ጄቶችን ለመስጠት ቃል እንደገቡላት ስቶልትንበርግ አስታውሰዋል፡፡


ዋና ፀሐፊው ይህም ታላቅ ድርሻ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



የየመን ሁቲዎች በኤደን ባህረ ሰላጤ በብሪታንያ መርከብ ላይ በሚሳየል ጥቃት ሰንዝረናል አሉ፡፡


ሁቲዎቹ እርምጃችን ምዕራባዊያኑ ሀያላን ለሚፈፅሙብን ጥቃት ምላሽ ነው ማለታቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


በቀጠናው የተሰማራው የአሜሪካ ባህር ሀይል ከኢራን ለየመን ሁቲዎች የሚሰጥ የጦር መሳሪያ ጭናለች ያላትን ጀልባ መያዙን እወቁልኝ እንዳለ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


ሁቲዎቹ በብሪታንያ መርከብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሰንዝረናል ቢሉም የተኮሱት መሳሪያ በመርከቧ አቅራቢያ ቢወድቅም ጉዳት አላደረሰባትም ተብሏል፡፡


ሁቲዎቹ እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ካላቆመች በቀይ ባህር የሸሪኮቿን መርከቦች እንመታለን በሚል አቋማቸው እንዲፀኑ ነው፡፡


እነ አሜሪካም የሁቲዎችን አለም አቀፍ ንግድን ከሚጎዳ ተግባር ለማቀብ የታለመ ነው ያሉትን ድብደባ እየፈፀሙባቸው መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የደቡብ አፍሪካዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እኛ የምንሟገተው ለፍልስጤማውያን ደህንነት መረጋገጥ እንጂ የሐማስ ጠበቆች አይደለንም አሉ፡፡


የናሌዲ ፓንዶር አስተያየት የተሰማው የእስራኤል ሹሞች የደቡብ አፍሪካ መንግስት የሐማስ ተወካይ ነው ካሉ በኋላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈፀመች ነው ስትል ደቡብ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ፍርድ ቤት መክሰሷ ይታወቃል፡፡


ከዚያን ጊዜ አንስቶ የእስራኤል እና የደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ጣራ እየነካ ነው ተብሏል፡፡


የደቡብ አፍሪካዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍልስጤማውያን የነፃ አገር ባለቤቶች እንዲሆኑ ከማገዝ ወደ ኋላ አንልም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ናሌዲ ፓንዶር አለምም ለዚህ መሰናዳት ይኖርበታል ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



Commentaires


bottom of page