top of page

የካቲት 5 2017 - በሐዋሳ ከተማ 1 ሊትር ቤንዚን ከ250 እስከ 350 እየገዙ እንደሚሰሩ የታክሲ እና የባጃጅ አሽከርካሪዎች ተናገሩ፡፡

በሐዋሳ ከተማ 1 ሊትር ቤንዚን ከ250 እስከ 350 እየገዙ እንደሚሰሩ የታክሲ እና የባጃጅ አሽከርካሪዎች ተናገሩ፡፡


ማደያዎች ነዳጅ የለንም እያሉ ቢሆንም በጥቁር ገበያ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑን ሰምተናል፡፡


መንግስት ከአንድ ወር በፊት አንድ ሊትር ቤንዚን በ101 ብር ከ47 ሳንቲም እንዲሸጥ ወስኖ የነበረ ቢሆንም ይህ ውሳኔ የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሐዋሳ ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም ተብሏል፡፡


ይህን ያሉን በከተማው የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡


በከተማዋ ለ25 ዓመት ያክል ማሽከርከራቸውን የነገሩን ታምራት በቀለ የተባሉ የታክሲ አሽከርካሪ በከተማው ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ #ቤንዚን በህጋዊ መንገድ ከማዲያዎች ማግኘት ቅንጦት ሆኗል ብለዋል፡፡


በከተማዋ ወደ 20 የሚጠጉ ማዲያዎች መኖራቸውን የተናገሩት አሽከርካሪው ከዚያ ወስጥ በአግባቡ የሚሰሩት ከ3 አይበልጡም እነሱም ከወሩ አጋማሽ ጀምሮ ወሩ መጨረሻ ላይ ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል አለቀ ይላሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ማደያዎች ቤንዚን አለቀ ይላሉ በህገ-ወጥ መንገድ ደግሞ ምርቱ እየተሸጠ ነው ይህ ከየት መጣ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡



ሌላው ለ9 ዓመት ያክል በከተማዋ የሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) አሽከርካሪ መሆናቸውን የነገሩን አቶ ቢኒያም ጢሞቲዮስ በከተማዋ በህጋዊ መንገድ ቤንዚን ማግኘት የማይታስብ በመሆኑ አብዛኛው በከተማዋ ያሉ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ የሚሞሉት ከህገ-ወጦች በሊትር 350 ብር ድረስ እየገዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


በከተማዋ ቤንዚን ከማድያዎች ማግኘት የማይታሰብ ነው ካለም በ #ሙስና እና በትውውቅ ነው የሚሉት ደግሞ በከተማዋ በተልምዶ ባጃጅ እየተባለ የሚጠራው በለሶስት እግር ተሽከርካሪ ለ6 ዓመት ማሽከርከራቸውን የነገሩን ደስታ የተባሉ አገልግሎት ሰጪ ናቸው፡፡


አቶ ደስታ ማደያዎች ነዳጅ በሞሉ በሁለተኛው ቀን አለቀ ይላሉ እያወጡ በህገወጥ መንገድ እየሸጡት ነው እንጂ እንዴት በመጣ በማግስቱ አልያም በሁለተኛው ቀን ያልቃል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


አሽከርካሪዎቹ ቤንዚን በህገወጥ መንገድ በውድ ስለሆነ የምንገዛው ለነዳጅ የምናወጣውን የምናካክሰው ተሳፋሪውን ከታሪፍ በላይ በእጥፍ እያስከፈልን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡


በተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ለመንግስት ብናቀርብም በቅርብ ይፈታል ይላሉ ችግሩ ግን እስካሁን አልተፈታም ይላሉ አሽከርካሪዎቹ፡፡


የሲዳማ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በከተማው ያለው የቤንዚን ችግር የጸጥታ ጉዳይ እስከመሆን መድረሱን ከወራቶች በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡


የክልሉ መንግስት ያለውን ችግር ለመፍታት ከወራቶች በፊት በክልሉ ርዕስ መስተዳደር የሚመራ ግብረ ሃይል አቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ችግሩ ሳይፈታ ኢትዮጵያ ከወጪ ገቢ የማያንስ ዶላር አውጥታ የምትገዛው ቤንዚን በህገ-ወጥ መንገድ በሲዳማ ክልል ዋና ከተማ ሃዋሳ ይቸበቸባል፡፡


በአማራ እና በትግራይ ክልሎችም ተመሳሳይ ችግር መኖሩ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…. https://tinyurl.com/6ufxu4xp


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page