ጃፓን የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ አገልግሎቶች እና ልማት የሚያደርገውን ስራ ለመደገፍ የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ተነገረ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ጃፓን ያደረገው የ15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ እና የምግብ ድጋፍ እንዲሁም የልማት ስራዎች የሚውል ነው ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጃፓን መንግስት ያደረገው15 ሚሊዮን ዶላር ወይም ወደ 1.9 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች በኢትዮጵያ አስቸኳይ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለመፍታት እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
ይህ የገንዘብ ድጋፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ለሰብአዊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት፣ የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር እና ዘላቂ ልማትን ለማጠናከር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግሯል።

7.7 ሚሊዮን ዶላር የሚገመተው የመጀመሪያው እርዳታ በሰብዓዊና በልማት ስራዎች ላይ ያተኩራል የተባለ ሲሆን ይህም በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚሰራበት ነው ተብሏል።
በጎርጎሮሳዊው በመጋቢት 2024 በተካሄደው የከፍተኛ ደረጃ የልማት ፎረም በኢትዮጵያ የሰብአዊ ምላሽ ለመስጠት የተለዩትን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የሰብአዊ ምላሽ ጉዳዮች ለመፍታት ያለመ ነው ተብሏል።
ድጋፉም በተባበሩት መንግስታት ውስጥ ያሉ IOM ፣ UNFPA፣ UNDP UNHCR እና ሌሎች በድርጅቱ ስር ያሉ ተቋማት በኢትትዮጵያ የሚከውኑትን ስራ ለመደገፍ እንደሚውል ተነግሯል፡፡
7.3 ሚሊዮን ዶላር የሚሸፍነው ሁለተኛው ድጋፍ ከዘጠነኛው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት ኮንፈረንስ (ቲካድ9) በፊት የጃፓን ፈጠራ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትብብር ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚውል ነው ተብሏል። እነዚህ ውጥኖች እንደ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ሴቶችና ወጣቶችን ማብቃት እና ዘላቂ የከተማ መስፋፋትን የመሳሰሉ አንገብጋቢ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የተነደፉ ናቸው ብሏል ድርጅቱ በላከልን መግለጫ።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚከወኑትም ከዩኤንዲፒ፣ UNFPA፣ UN-Habitat፣ ዩኒሴፍ፣ የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የአቅም ግንባታ ኢንስቲትዩት እና WFP ጋር በመተባበር ነው ብሏል።
አስቸኳይ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለመሙላት ተፈናቃይ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እና የረጅም ጊዜ የልማት ችግችን ለመፍታት የጃፓን መንግስት እና ህዝብ ለኢትዮጵያ ላሳዩት ልግስና እና ድጋፍ በተባበሩት መንግስታት ረዳት ዋና ጸኃፊና በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ እንዲሁም እርዳታ አስተባባሪ ዶ/ር ራሚዝ አላክባሮቭ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጃፓን አጋርነት በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ህይወት ለማሻሻል እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት ወሳኝ የሆኑ ሰብአዊ ቀውሶችን ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው በመግለጫው ተጠቅሷል።
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5rs
Comments