ስዊድን በይፋ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) አባል ሆነች፡፡
ስካንድኔቪያዊቱ አገር በይፋ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ 32ኛ አባል አገር የሆነችው በአሜሪካ ዋሽንግተን በተከናወነ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ስዊድን የኔቶ አባል የሆነችው በቅርቡ የሐንጋሪን ድጋፍ ካገኘች በኋላ ነው፡፡
አገሪቱ ለዘመናት ስትከተለው የነበረው ወታደራዊ ገለልተኝነት አብቅቷል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ ጄንሰድ ስቶልትንበርግ ስዊድን በይፋ የድርጅቱ አባል መሆኗን ታሪካዊ ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ጎረቤት ፊንላንድም ካለፈው አመት ሚያዚያ ወር አንስቶ የኔቶ አባል እንደሆነች ዘገባው አስታውሷል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ሱዳን በአጣዳፊ ተኩስ እንዲቆም ወሰነ፡፡
ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው በሱዳን በረመዳን የፆም ወቅት ተኩስ እንዲቆም ለማድረግ አልሞ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
የሱዳን መንግድት ጦር እና RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ ከ10 ወራት በላይ ሆኗቸዋል፡፡
ምክር ቤቱ በሱዳን የረመዳን ወቅት የተኩስ አቁም እንዲደረግ የወሰነው በ14 ድጋፍ እና በ1 ድምፀ ተአቅቦ መሆኑ ታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ከተኩስ አቁም በተጨማሪ ያለ አንዳች መሰናክል ለህዝቡ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ መጠየቁ ታውቋል፡፡
የሱዳን ጦርነት የመቆም ምልክት አይታይበትም፡፡
ጦርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰው ነው ተብሏል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግስት አገሪቱ ከሞዛምቢክ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር የአጥር ግንብ እየገጠገጠበት ነው፡፡
የድንበሩ አካባቢ በግንብ የሚታጠረው በተለይም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተሰርቀው ወደ ሞዛምቢክ የሚወሰዱ መኪኖች እንዳያልፉ ለማገድ ታልሞ እንደሆነ ዲፌንስ ፖስት ፏል፡፡
እጅግ አስፈላጊ በሆኑ መተላፊያዎች ላይ 25 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የግንብ አጥር እንደሚገጠገጥ ታውቋል፡፡
የግንብ አጥሩን ለመገጥገጥ የደቡብ አፍሪካ መንግስት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የግንቡ ስራ በተጠናቀቀባቸው ስፍራዎች ከወዲሁ መልካም ውጤት እንደተገኘበት በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments