top of page

የካቲት 30፣2016 - ከመጋቢት 22፣2015 ዓ/ም በፊት የባንክ ፈቃድ የተሰጠባቸው ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ተፈቀደ

ተሽከርካሪዎቹ እና እቃዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ የተፈቀደውም በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል የሚቀርቡ ሠነዶች አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎባቸው ነው ተብሏል።


ይህም የሚሆነው ለመጨረሻ ጊዜ  መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለጉምሩክ ኮሚሸን ከፃፈው ደብዳቤ ላይ ተመልክተናል።


የውጪ ምንዛሬ ፈቃድ ክልከላ በተደረገባቸው እቃዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ ማስተካከያ መደረጉን በመጥቀስ በሚኒስትር ድኤታው እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የተፃፈ ደብዳቤን ሸገር ተመልክቷል።


ተሽከርካሪን ጨምሮ 28 ምርቶች ከጥቅምት 4፣2016 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የውጭ ምንዛሬ እንደይፈቀድላቸው መወሰኑ ይታወሳል።


የውጭ ምንዛሬ ክልከላ ከተደረገባቸው እቃዎች ጋር ተያይዞ በአፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት ማስተካከያ ተደርጓል ተብሏል፡፡


በጥቅምት ወር በወጣው እና የውጭ ምንዛሬ የማይፈቀድላቸው 38 ዝርዝሮች ውስጥ የተካተቱ ምርቶች የሆኑ ግን ደግሞ ምርቶቹ እና ተሽከርካሪዎቹ በሕግ በተደነገገ ፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ ከሆነ  በተደረገው ማስተካከያ ክልከላው አይመለከታቸውም ተብሏል።

ተሽከርካሪዎች ጎረቤት አገር ወደብ ወይም ጉምሩክ ጣቢያ በደረሱበት ጊዜ በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ (ማሻሻያ) ቁጥር 1287/2015 አንቀጽ 2(24) ለአዲስ ተሽከርካሪ የተሰጠውን ትርጉም የሚያሟሉ ሆነው ነገር ግን ይህን ውሳኔ ሲጠብቁ የተሽከርካሪው እድሜ ያገለገለ ምድብ ውስጥ የገባባቸው ከሆነ በክልከላው ምክንያት በጎረቤት አገር ወደብ ወይም በጉምሩክ ጣቢያ የቆዩበት ጊዜ ሳይታሰብ እድሜው ጎረቤት አገር ወደብ ወይም የጉምሩካ ጣቢያ እስከደረሰበት ያለውን ጊዜ ድረስ ብቻ በማስላት እንዲስተናገዱ ማስተካከያ ተደርጓል።



የቀረጥ ነፃ ሱቆች የሚያስመጧቸው ዕቃዎች የውጭ ምንዛሪ ክልከላው እንደማይመለከታቸው ማስተካከያውን የሚያስረዳው ደብዳቤ ላይ ተጠቅሷል።


የገንዘብ ሚኒስቴር የውጪ ምንዛሬ ክልካላው በተመለከተ በጥቅምት ወር 2015 ዓ/ም የተጻፈው ደብዳቤ እና በተለያየ ጊዜ የተሰጡ ማብራሪያዎች መሻራቸውንና በማስተካከያው መሰረት ተፈፃሚ እንዲሆን መወሰኑን ከደብዳቤው ላይ ተመልክተናል።


ንጋቱ ሙሉ

Yorumlar


bottom of page