top of page

የካቲት 29፣2016 - ከ5 ዓመት በፊት በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ላለፈ ሰዎች መታሰቢያ ተገነባላቸው

Updated: Mar 9, 2024

ከዓምስት ዓመት በፊት መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ንብረትነቱ የኢትዮጵያ የሆነ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ከቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ አደጋ አጋጥሞት በመከስከሱ የ159 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡


ከእነዚህ ሕይወታቸው ካጡ ሰዎች መካከል ለ18ቱ አደጋው በደረሰበት አካባቢ መታሰቢያ እንደተገነባላቸው ተነግሯል፡፡


የተገነቡት መታሰቢያዎች የትምህርት ቤት፣ የውሃ እንዲሁም የጤና ተቋማት ናቸው ተብሏል፡፡



በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ የተገነቡት እነዚህ የመታሰቢያ መሰረተ ልማቶች 125 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸውም ሰምተናል፡፡


ከፕሮጀክቱ ወጪ 100 ሚሊዮን ብሩ በቦይንግ ማህበረሰብ ኢንቨስትመንት ፈንድ(BCIF) የተሰጠና ቀሪውን ብር በአለም አቀፉ የካቶሊክ የተራድኦ ድርጅት(CRS) እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ክ የተሸፈነ ነው ተብሏል፡፡




መታሰቢያ የት ይገንባላቸው ተብለው ከተጠየቁት የ159 በአደጋው ህይወታቸው ካጡ ሰዎች ቤተሰቦች መካከል፤ የ18ቱ ቤተሰቦች መታሰቢያው እዛው አደጋው በደረሰበት አካባቢ እንዲሆን እንደፈቀዱም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ክ የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በቀለ ሞገስ ነግረውናል፡፡


አደጋው በደረሰ ጊዜ የአካባበው ማህበረሰብ ያሳዩት ሰብዓዊነት እና እንደ ባህላቸው በተለያየ ጊዜ ያደረጉት የሀዘን ስነ ስርዓት እነዚህ ቤተሰቦች መታሰቢያው በአካባቢው እንዲሰራ ፈቃዳቸው የሰጡበት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡


በትናንትናው እለት የተመረቁት እነዚህ የመታሰቢያ ፕሮጀክቶች፤ እያንዳንዳቸው 4 ብሎክ ያላቸው ሁለት ከ1 – 8ተኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች ከነ አስፈላጊው ቁሳቁሶቻቸው፣ 13,852 ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና በ37 ኪሎ ሜትር ላይ የተዘረጋ የመጠጥ ወሃ እንዲሁም 1 ጤና ኬላ ናቸው ሲሉም አቶ በቀለ አውርተውናል፡፡



ማንያዘዋል ጌታሁን



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


bottom of page