top of page

የካቲት 28 2017 - በኢትዮጵያ ከሚወለዱ ህፃናት የልደት ምዝገባ የሚያደርጉት 37 በመቶቹ ናቸው ተባለ

በኢትዮጵያ ከሚወለዱ ህፃናት የልደት ምዝገባ የሚያደርጉት 37 በመቶቹ ናቸው ተባለ፤ በሀገሪቱ ከሚከሰቱ ሞቶች ደግሞ 16 በመቶቹ ብቻ እንደሚመዘገቡ ተነግሯል፡፡


ለዚህም የተሟላ የዜጎች የጤና መረጃ እንዲኖርና የውልደት፣ ሞት እንዲሁም ሌሎች ከስነ-ህዝብ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል፡፡


በሀገሪቱ በጤና ተቋማት ከሚመዘገቡ ሞቶች ውጪ አብዛኛዎቹ ምክንያታቸው እንደማይመዘገብ እና ይህም ለበሽታ መከላከልና የጤና ጥበቃ ስራዎች ላይ ተጽእኖ አለው ተብሏል፡፡


ፕሮጀክቱ ይህንን ክፍተት ይሞላል የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች በመለየት የዳሰሳ ጥናቶች በማካሄድ እና መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን ወቅታዊ የጤና ስጋቶችን ለይቶ ለማወቅ ያስችላል ተብሏል፡፡


#Impact_HDSS_Ethiopia የተባለው ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በልደት ሞትና የሞት መንስኤዎች ላይ መረጃን መሰብሰብ እና ጥቅም ላይ በመዋል የሚቀረፁ የጤና ፖሊሲዎች በተረጋገጠ መረጃዎች ላይ ተመስርተው እንዲሰሩ ያደርጋል ሲል በኢትዮጵያ በህብረተሰብ ጤና ላይ የሚሰራው አለምአቀፉ ቫይታልስትራቴጂስ ተናግሯል፡፡


በአገሪቱ በሚገኙ 13 የጤና እና ስነ ህዝብ ክትትል ጣቢያዎች እያንዳንዳቸው ከሃገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማገናኘት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የብረተሰብ ክፍሎችን የሚሸፍን ጥናት ይካሄዳል ተብሏል፡፡


ጥናቱ ስለ ዜጎች የጤና ሁኔታ ጥልቅ ግንዛቤን በመስጠት በመላ ሀገሪቱ የጤናና የስነ ህዝብ መረጃ ለመከታተል ወሳኝ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከጣቢያዎቹ የሚገኘውን መረጃም ከብሄራዊ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት ጋር በማገናኘት ስለወሊድ ሞትና የሞት ምክንያት ጥራት ያለው መረጃ ለጤና ጥናትና ምርምር እንዲሁም የፖሊሲ ውሳኔዎችን ለማሳወቅ ያስችላል ተብሏል፡፡


ኢትዮጵያ የህዝቧን የጤና መረጃ በመሰብሰብ እና በማጠናቀር በስነ ህዝብ መረጃዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝ የብሔራዊ መረጃ አስተዳደር ማዕከል የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አስናቀ ወርቁ ተናግረዋል፡፡


የቫይታልስትራቴጂ ፕሬዝዳንትና ዋና አስፈጻሚ ሜሪ አን አቲቤት በበኩላቸው ሁሉን አቀፍ አካታችና ዘላቂነት ያለው የህዝብ ጤና ስርዓቶች በጠንካራ የሲቪል ምዝገባና ስታትስቲክስ ምዝገባ ላይ የተመሰረቱ ናቸው ብለዋል፡፡


ለዚህም የኢትዮጵያን የጤና መረጃ ስርዓት ለማጠናከርና የብረተሰብ ጤና ለማሻሻል የሚያግዘውን ፕሮጀክት በመደገፋችን ደስ ይለናል ብለዋል፡፡


በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ በላይ ሃገራት ሙሉ በሙሉ የሚሰሩ የሲቪል ምዝገባና ወሳኝ የስታትስቲክስ መረጃዎች እንደሌላቸው የተነገረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ልደት ሞትና የሞት መንስኤን መመዝገብ ላይ ያለው ቁጥር ከሚጠበቀው በታች መሆኑ ተነግሯል፡፡


በሀገሪቱ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ውልደት ያልተመዘገበ ሲሆን ከስድስት መቶ ሃምሳ ሺህ በላይ ሞቶች ደግሞ ምክንያታቸው የማይታወቅ እና ያልተመዘገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መረጃ ያሳያል፡፡


ፕሮጀክቱ ከጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በጤና ሚኒስቴር ፣በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በብሔራዊ መረጃ አያያዝ ማዕከልና በሌሎችም ተቋማት የሚተገበር ሲሆን ለሶስት አመታት እንደሚዘልቅ ተጠቅሷል፡፡


ምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page