በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ለተመዘገበው የጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ ማስፋፊያ ቃል የተገባው ገንዘብ በታቀደው ጊዜ መሰብሰብ ባለመቻሉ፤ የማስፋፊያ ስራውን እንዳዘገየው ተነገረ፡፡
ለጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ ማስፋፊያ ተብሎ በተለያየ አካላት 240 ሚለዮን ብር ቃል የተገባ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ የተሰበሰበው ብር 20 ሚሊዮን ብቻ ነው ተብሏል፡፡
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የዲዛይን ስራ ሙሉ በሙሉ ቢጠናቀቅም ለስራው ይውላል ተብሎ ቃል የተገባው ገንዝብ አሰባሰብ ቀርፋፋ እንደሆነ ለሸገር የተናገሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ናቸው፡፡
ክልሉ እንደ አዲስ ሲዋቀር የተፈጠረው ክፍተት እና ቃል የገቡ አካላት ገንዘቡን በጊዜ ገቢ አለማድረጋቸው፤ የገንዘብ አሰባሰቡ በታሰበው ፍጥነት እንዳይራመድ ካደረጉት መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑም የቢሮው ሀላፊ አስረድተዋል፡፡
‘’ምንም እንኳ ከታቀደው ብር 12 በመቶው ብቻ ገቢ ቢሆንም የማስፋፊያ ፐሮጀክቱ ግንባታ በቅርቡ ለመጀመር እየበረታን ነው’’ ሲሉም አቶ መንገሻ ተናግረዋል፡፡
ከጢያ ትክል ድንጋይ ቅርስ መገኘት ያለበት ገቢ እየተገኘ አይደለም’’ ያሉን ሀላፊው፤ ለዚህም በተገቢው ልክ ቅርሱን የማስተዋውቅ ስራ ባለመሰራቱ እንዲሁም ከቅርሱ አጎራባች ቦሆኑ ቦታዎች ያለው የፀጥታ ስጋት እንደ ዋነኛ ምክንያቶች ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ መንገሻ በተለይም ቱሪሰቶች ያለስጋት ወደቦታው መጥተው እንዲጎበኙ አጎራባች ከሚገኘው ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር እየተነጋገርን ሲሆን የማስተዋወቁንም ስራ አበርትተን ለመስራት አቅደናል ሲሉም አውርተውናል፡፡
ከ12ኛው እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን እንደተተከለ የሚነገርለት የጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ በ1972 ዓ.ም በዩኔስኮ የተመዘገበ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ82 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘ ነው፡፡

ማንያዘዋል ጌታሁን ያሰናዳውን በማርታ በቀለ

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments