top of page

የካቲት 26 2017 - ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ 90 በመቶው ተገቢው ህክምናና ማጣራት ሳይደረግ ወደ ወንዞች የሚለቀቅ መሆኑ ተነገረ

  • sheger1021fm
  • Mar 5
  • 2 min read

በአዲስ አበባና አካባቢዋ ካሉ ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ 90 በመቶው ተገቢው ህክምናና ማጣራት ሳይደረግ ወደ ወንዞች የሚለቀቅ መሆኑ ተነገረ፡፡


ይህም እስከ ታችኛው ተፋሰስ ድረስ የውሃ ብክለት እያስከተለ ሰዎችንም ለተለያየ የጤና ችግር እያጋለጠ መሆኑን የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ተናግሯል፡፡


ከባለስልጣን መ/ቤቱ ሰነድ ላይ እንደተመለከትነው ተጣርተዋል ተብለው የሚለቀቁ ፍሳሽ ቆሻሻዎች እንኳን በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት ያልተጣሩና የተለያዩ ባክቴሪያዎችን የያዙ ሆነው በመገኘታቸው በተለይ ለእርሻ ስራ መዋል የሌለባቸው ናቸው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ግን በአዲስ አበባ በወንዝ ዳርቻዎች እንደ ጎመንና ቆስጣ እንዲሁም ሰላጣና መሰል የጓሮ አትክልቶች ተመርተው ለነዋሪው ይቀርባሉ፡፡


ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ 76ቱም ወንዞች ከመኖሪያ ፣ ከኢንዱስትሪ ፣ ከሆስፒታል እና ከሌሎችም በሚለቀቁ ፍሳሽ ቆሻሻዎች በተለያዩ ኬሚካሎችና በሽታን በተላመዱ ባክቴሪያዎች ጭምር የተበከሉ ናቸው፡፡


የተወሰደው ናሙናም እንደሚያሳየው በውሃው ውስጥ እንደ ሰልፌት፣ ክሮሞየም ፣ ያሉና ሌሎችን ኬሚካሎች እና በሽታ የተለማዱ ባክቴሪያዎችም ተገኝተውበታል፡፡


ይህም እንደ አተት ፣ ጃርዲያና ኮሌራ ላሉ የተላላፊ በሽታዎች ከማጋለጡ በተጨማሪ ውሃውን ተጠቅመው በሚያመርቷቸው ምግቦችም ስለሚበከሉ የጨጓራ ግድግዳ ካንሰርን ጨምሮ ለቆዳና የነርቭ ካንሰር ያጋልጣሉ ተብሏል፡፡


የካንሰር የአንጎልና የኩላሊት ጉዳትም የሚያስትሉ ኬሚካሎችም እንዳሉባቸው ተረጋግጧል ተብሏል፡፡

ወደ ወንዞች የሚለቀቁ ኬሚካሎችንም የያዙ ፍሳሽ ቆሻሻዎች በውሃ ላይ በሚፈጥሩት ብክለት በአዲስ አበባ ብቻ በአመት ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች በተቅማጥ እንዲያዙ ከመካከላቸው 467 ያህሉም ሕይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ይሆናል መባሉን ሰምተናል፡፡


የአለም ባንክን መረጃ ዋቢ አድርጎ የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እንዳለው በውሃ ብክለት ምክንያት በሽታ በመተንፈሻ አካላት ችግር በየአመቱ በአዲስ አበባ ብቻ 219 ሰዎች ይታመማሉ 57ቱም ሕይወታቸው ያልፋል፡፡


በሌላ በኩል ይኸው ችግር በሚያስከትለው በወባና በመሰል በሽታም 35 ሰዎች በየአመቱ እንደሚሞቱ ከሰነዱ ተመልክተናል፡፡


በአዲስ አበባና አካባቢዋ 65 በመቶው የሃገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ የተባለ ሲሆን 90 በመቶዎቹ ደግሞ ፍሳሽ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ በአቅራቢያቸው ወዳለ ወንዝ ይለቀቃሉ ተብሏል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page