ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የምትልከው ዓመታዊ ምርት፤ ኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ከምትልከው በእጥፍ ያንሳል ተባለ፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ እንደ እ.አ.አ በ2023 ምርቶችን ልካ ያገኘችው ገቢ 58 ሚሊዮን ዶላር ነው የተባለ ሲሆን በተመሳሳይ ዓመት ኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ምርቶቿን ልካ ያገኘችው ገቢ 112.4 ሚሊዮን ዶላር ነው ተብሏል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ እስካሁን 200 ሚሊዮን ዶላር መድረስ እንዳልቻለ ተነግሯል፡፡
ይህ የተነገረው ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያና የኬንያ የንግድ ፎረም ላይ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዮሐንስ ፋንታ የኢትዮጵያና የኬንያ ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ልካ በ2023 ያገኘችው ገቢ 58 ሚሊዮን ዶላር እንደማይሻገር የተናገሩት አምባሳሩ በተመሳሳይ ኬኒያ ወደ ኢትዮጵያ ከላከችው ምርት 112.4 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች ብለዋል፡፡
ይህም የሁለቱ ሀገራት ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተው ይህን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ በዋኝነት የምትልካቸው ምርቶች ቡና ፣ ቅመማ ቅመም ፣ የቆዳ ውጤቶች እና የኤሌክትሪክ ግብአቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ኬንያ ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ ረዥም ታሪካዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም አመታዊ የንግድ ልውውጣቸው ግን ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡
ይህን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆን የማክሮ ኢኮኖሚን ማሻሻያን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው ስለዚህ የኬንያ ወጣቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፀሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ኬኒያ ረዥም ታሪክ እንዳላቸው ተናግረው ይህም ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ንግድ መለወጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በኬኒያ መንግስት አማካኝነት የተሰናዳው የኢትዮ ኬኒያ የቢዝነስ ኮንፈረንስ ለ5 ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ተነግሯል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments