top of page

የካቲት 25 2017 - ታሪክን የኋሊት - በኢትዮጵያ የዛሬ 50 ዓመት በዛሬው ቀን የገጠር መሬት አዋጅ ታወጀ

  • sheger1021fm
  • Mar 4
  • 2 min read

በኢትዮጵያ የዛሬ 50 ዓመት በዛሬው ቀን የገጠር መሬት አዋጅ ታወጀ፡፡


የካቲት 25 ቀን 1967 የወጣው የመሬት አዋጅ ከዚያ በፊት ሰፍኖ የቆየውን የመሬት አጠቃቀምና ስሪት ለውጦ ከባለርስቱ ወደ አራሹ ገበሬ ያዛወረ አዋጅ ነበር፡፡


የመሬትን ባለቤትነት ላራሹ የማድረግ አስፈላጊነት ጥያቄ በጊዜው ለነበረው ንጉሳዊ መንግስት ከተለያዩ ክፍሎች ሲቀርብ ቆይቷል፡፡


ገበሬዎች በሰላማዊና በአመፅ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡


የጊዜው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በተደራጀ መልኩ በአመፅ ጥያቄውን ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡


በኢትዮጵያ ያለው የመሬት ስሪት፣ በርስትነት በገባርነት የሚያዝ ሆኖ ቆይቷል፡፡

መሬት በአብዛኛው ትውልድ ቆጥሮ ወይም በውርስ የሚይዙት፣ ሲሆንም ነባሩን ነዋሪ አፈናቅሎ በአገልግሎትና በስጦታ የሚሰጥ ይዞታ ነበረው፡፡


በአገልግሎትና በስጦታ በሰፊው የሚያዘው መሬት ፣ ነባሩን ገበሬ ከይዞታው የሚያፈናቅልና ጭሰኛ ሆኖ በባለርስቱ ፈቃድ ብቻ የሚጠቀም አድርጎታል፡፡


በቀድሞው ዘመን በአስተዳዳሪነት፣ ሃገር ለመጠበቅና ፀጥታ ለማስከበር የተመደቡ ለዘመቻ ተነሱ በተባሉ ጊዜ ፣ ሃገር ለሚጠብቁ #ጠመንጃ_ያዥ_ወታደሮች ፣ መሬት ማደሪያቸው እንዲሆን ይሰጣቸዋል፡፡


ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ፣ ዘመናዊ አስተዳደር ሲተካ፣ ቀድመው በውትድርና መሬቱን የያዙት አገልግሎታቸው ቢቋረጥም፣ መሬቱን በርስትነት ይዘው መጠቀም ቀጠሉ፡፡


በመሬቱ ላይ የነበረውም ገበሬ፣ በጉልበት የሚያገለግላቸው ወይም ካመረተው ገሚስና ሲሶ እየሰጠ የሚኖር ሆነ፡፡


ባለርስቱ ሳይደክምና መሬቱ ካለበት ዘንድ መሄድ ሳያፈስልገው የመሬቱ ፍሬ እስካለበት ድረስ ይወሰድለታል፡፡ ጭሰኛውን ከፈለገ ይነቅለዋል፡፡


ሰፋፊ መሬቶች በጥቂት ሰዎች በመያዛቸው የገበሬው ብሶትና እሮሮ በየቀኑ እየተባባሰ ሄደ፡፡

የካቲት 1966 ዓ/ም ፣ የህዝብ አመፅ መነሻ አድርጎ የተነሳው የመሬት ላራሹን ጥያቄ ነበር፡፡


አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ከገበሬው ማህበረሰብ የወጡ ስለነበሩ የገበሬውን እንግልትና ብሶት ስለሚረዱ ሰፊ ትግል ለማድረግ አነቃቅቷቸዋል፡፡


ወታደራዊ ደርግ፣ ዘውዳዊውን ሥርዓት አስወግዶ ሥልጣኑን በእጁ ሲያደርግ ግን የመሬት የተጠቃሚነት ሥርዓት መለወጥ ቀዳሚ ተግባሩ አደረገ፡፡


ለውጡን ከኋላ ሁነው ይገፉ የነበሩት፣ በዚያን ጊዜ ተራማጅ ይባሉ የነበሩ ወጣቶችም፣ አዋጁ ተፋጥኖ እንዲታወጅ አስዋፅኦ አድርገዋል፡፡


ሕዝባዊው #አብዮት በፈነዳ በዓመቱ የካቲት 25 ቀን 1967 የገጠር መሬትን ለሕዝብ ያደረገው አዋጅ ታወጀ፡፡


በዚያ አዋጅ መሬት ባለርስት ነኝ ከሚለው ሙሉ በሙሉ ተወስዶ ለሚያርሰው ገበሬ እንዲሆን ተረጋገጠ፡፡


የየካቲት 25ቱ የመሬት አዋጅ ፣ ባላባቱን ከጥቅሙ ጋር አቆራርጦ ፣ባዶ እጁን ሲያስቀረው #ጭሰኛና ደሃ ገበሬዎችን የመሬት ባለቤት አደረጋቸው፡፡


አዋጁ ፣ መሬት የህዝብ መሆኑንና ገበሬው እስከ 10 ሄክታር ድረስ እንደሚያገኝ ይደነግጋል፡፡


ነገር ግን በአዋጁ መሰረት ለገበሬው አልተሰጠም፡፡


ገበሬው የመሬቱ ባለቤት ሆነ ቢባልም ግን ፣ አዋጁ የመሸጥና የመለወጥ መብቱን ገድቦታል፡፡


ገበሬው የመሬት ቋሚና ሙሉ ባለመብት አለመሆኑና በየጊዜው እየተሸነሸነ መሰጠቱ ለምርታማነት መቀነስና ለገበሬውም ቅሬታ ምክንያት መሆኑ በየጊዜው ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡


እንዲያም ሆኖ የዛሬ 50 ዓመት በዛሬው እለት የታወጀው የገጠር መሬት አዋጅ ፣ የቀደመው ሥርዓት ዋነኛ የኢኮኖሚ መሰረት የነበረውን መሬት ከመሬት ባላባቶች በመንጠቁ የአብዮቱ ዋነኛ ጥያቄ ምላሽ ብቻ ሳይሆን የሥርዓተ ማህበር ለውጡ ማህተም ተደርጎ ይታወሳል፡፡


እሸቴ አሰፋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page