‘’አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ’’ በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ የወጣቶች የሰላም ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መርሀ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እየተከናወነ ይገኛል።
የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ ወጣቶች በሀገራዊ አንድነት፣ ሰላም፣ በጋራ እሴቶች እና በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ በመጨበጥ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖራቸውን ንቁ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሆነ በመድረኩ ተነግሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመዝጊያ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ‘’ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ እንድትደርስ አባቶች በአድዋ ጦርነት በጋራ የከፈሉት መስዋዕትነት ትልቅ ነው’’ ብለዋል፡፡
የአድዋ ድል የተገኘው በኢትዮጵያውያን በጋራ በተሰራ ስራ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የሚታዩ የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት አብሮ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
‘’ሀገር የምትቆመው በጋራ እና በህብረት ሲሰራ ነው’’ ያሉ ሲሆን ‘’ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚህ ሊሰራ ይገባል’’ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
‘’ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው አብረው በጋራ የዘመቱት ለሀገር የነበራቸው ፍቅርና አንድነት ስለነበር ነው’’ የሚሉት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ‘’ሀገር እንድትቀጥል ካስፈለገ ከመሪዎች ጋር ያለን ጠብ ቀደ ጎን ማለትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
‘’ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ሀገርን ወደ ፊት ማስቀጠል አይቻልም’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‘’የሀገሪቱ ሰላም እንዲመለስ የተሻለ እድገት ለማስመዝገብ እንደ አድዋ ጀግኖች በጋራ መስራት ይጠበቃል’’ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ አሳስበዋል፡፡
የአድዋ ድልን በተመለከተ የሚዘክሩ የተለያዩ የጥበብ ስራዎች አለመሰራታቸውን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘’የታሪክ ፀኃፊዎችና የጥበብ ሰዎች ስለአድዋ ትውልዱ እንዲማርበት የተለያዩ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል’’ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments