የካቲት 19 2017 - የደቡብ ሱዳኖቹ ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃት ቀንሷል ሲል የጋምቤላ ክልል ተናገረ
- sheger1021fm
- Feb 26
- 1 min read
ከዚህ ቀደም መነሻቸውን ከደቡብ ሱዳን ያደረጉ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል።
አሁን ግን በአመዛኙ ካለፉት ዓመታት አኳያ ጥቃቱ እየቀነሰ መጥቷል ሲል ክልሉ ተናግሯል።
#የጋምቤላ_ክልል የመንግስት ኮሚዮኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጌሌጅሎ ባለፉት ዓመታት በድንበር አዋሳኝ ባሉ ቀበሌዎች በርካታ ህጻናትና የቁም እንስሳት በታጣቂዎች እንደሚወሰዱ እና ጥቃት እንደሚደርስ አንስተው አሁን ላይ ግን ጥቃቱ ቀንሷል ብለዋል።
አቶ ኡጁሉ ጥቃቱ ቀንሷል ይበሉ እንጂ አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለመሆኑም ነግረውናል።

ግን ይሄ እንቅስቃሴ ያን ያህል ስጋት ላይ አይጥልም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በክልሉ በእነዚህ ታጣቂዎች ምክንያት በርካታ ጉዳት ደርሷል።
ክልሉን እና አካባቢውን የሚጠብቁ የፌዴራል ፖሊስና መከላከያ ሰራዊት አሉ ።
ሆኖም እነሱ ባሉበት ሁኔታ ህፃናትና እንስሳት በታጣቂዎቹ ሲጋዙ እና ጉዳት ሲደርስባቸው ነበር።
ምክንያቱስ ምንድን ነው? ብለን ለአቶ ኡጁሉ ላነሳንላቸው ጥያቄ ታጣቂዎቹ በትናንሽ ቡድኖች ተበታትነው በተለያዩ አቅጣጫዎች ስለሚንቀሳቀሱ ነው የሚል ምላሽም ሰጥተውናል።
ፍቅሩ አምባቸው
Kommentare