የካቲት 17 2017 - ‘’የአፍሪካ ወጣቶች በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን፤ በሀገራቸው የፖለቲካ ጉዳይና የነገ ዕጣ ፋንታ ላይ እንዲመክሩ ማድረግ ይገባል’’
- sheger1021fm
- Feb 24
- 2 min read
ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ጎን ለጎን የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ እንዲካሄድ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ33 ሀገራት ወጣት ተወካዮች ሊጠይቁ ነው፡፡
የአፍሪካ ወጣት ተወካዮች ከህብረቱ የመሪዎች ስብሰባ ጎን ለጎን የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ እንዲካሄድ የሚጠይቀውን እና የሁሉም ሀገራት ተወካዮች ፊርማቸውን ያኖሩበትን ሰነድ ለህብረቱ በዚህ ሰሞን ሊያስረክቡ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ይህን የተመለከተ እና የአህጉሩ ወጣቶች በሀገራቸው ፖለቲካ ጉዳይ ሊኖራቻው ስለሚችለው ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
በጉባዔው ላይ ከ33 የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል የተባለ ሲሆን በነገው እለት እንደሚጠናቀቅ አዘጋጆቹ ነግረውናል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ስራ አስኪያጅ እና የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ አስተባባሪ የሆኑት እንጂነር ጫላ አሰፋ በየዓመቱ ከሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ጎን ለጎን በህብረቱ እውቅና ያለው የወጣቶች ዓመታዊ ጉባዔ እንዲካሄድ የሚጠይቅ የሁሉም ሀገራት ተወካዮች ፊርማ ያለበት ሰነድ ለህብረቱ አዲሱ ኮሚሽነር እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ መካሄዱ ወጣቱን ያገለለ እንደሆነ የሚነገርለትን የአህጉሩን ፖለቲካ ለማረቅ እንደሚረዳ ተነግሯል፡፡
የአፍሪካ ወጣቶች በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ እና የነገ ዕጣ ፋንታ ላይ ለመምከር እንዲሁም ወይይትን ባህል ለማድረግ በየመቱ በህብረቱ የሚደረግ ጉባዔ ያስፈልጋል ሲሉ ኢ/ር ጫላ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ከፖለቲካ የተገለለው እና ለጦር ሜዳ ብቻ የሚፈለገውን ወጣት በሀገሩ እና በአህጉሩ ጉዳይ እንዲወያይ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተነግሯል፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩ የቀድሞ የአህጉሩ መሪዎች አፍሪካን ቢያንስ በአንድ ጥላ ስር መነጋገር እንድንችል ያደረጉት ነገር እና የሄዱት ርቀት የሚበረታታ እንደሆነ የጠቆሙት የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ስራ አስኪያጅ እና የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ አስተባባሪ የሆኑት ኢ/ር ጫላ አሰፋ እኛም ዛሬ ያን ተቀብለን አፍሪካ ይበልጥ ወደ አንድ እንድትመጣ መርዳት አለብን ብለዋል፡፡
ችግሮቻችንን እኛ መፍታት ባለመቻላችን ሌላ አካል ነው እየፈታልን ያለው ያሉት ኢ/ር ጫላ አሰፋ ይህን ማስቀረት አለብን እንዴት ከተባለ በመወያየት እና ወጣት መሪዎችን በማምጣት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካን ወጣት ወደ ፖለቲካው እንዲገባ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መወሰን እና መምራት እንደሚችሉ ጭምር ማድረግ ያስፈልጋል ያን ማድረግ ሲቻል በአህጉሩ ባሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች የሚሳተፈውን እና ተጠቂ የሆነውን ወጣት ማትረፍ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ33 ሀገራት ጦርነት እና እርስ በርስ ግጭት እንዳለ የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡
በጦርነቱ ዋነኛው ተሳታፊው እና ተጎጂውም ወጣቱ ነው ተብሏል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comments