top of page

የካቲት 14፣2016 - ወርልድ ቪዥን በ27 የአፍሪካ ሀገራት ስራ ላይ ለሚያውለው ፕሮግራም 1.7 ቢልየን ዶላር መመደቡን ተናገረ

ወርልድ ቪዥን የህጻናት ረሃብ እና ያልተመጣጠነ አመጋገብን ለመቅረፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ27 የአፍሪካ ሀገራት ስራ ላይ ለሚያውለው ፕሮግራም 1.7 ቢልየን ዶላር መመደቡን ተናገረ፡፡


ይፋ የተደረገው ገንዘብ በምስራቅ፣ በምዕራብ እና በደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል።


በወርልድ ቪዥን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካርማን ቲል ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ላይ አሁን የሚታዩ ቀውሶች በህፃናት አማጋገብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው ብለዋል፡፡


በተለይ ህፃናት ብቁ ተማሪ እንዲሆኑ የተመጣጠነ ምግብ ዋነኛ መሰረት ነው ያሉ ሲሆን አሁን ለ3 ዓመት የሚተገበረው ፕሮጀክትን በመጠቀም ለጋሽ አካላት እና ባለድርሻ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ህፃናት የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ ለማድረግ የሚሰራው ስራ እንዲያግዙ እንሰራለን ብለዋል፡፡


የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው መንግስት ባለው አቅም ልክ የህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡


ወርልድ ቪዥን እንደ አፍሪካ የሚተገብረው፤ የህፃናት ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ችግር ለመፍታት በሚሰራው ስራ የኢትዮጵያ መንግስት የተጠቃሚዎችን መለየት ላይ አብሮ ይሰራል ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ መንግስት ህፃናት የተመጣጠነ ማዕድ አንዲቆርሱ፣ እናቶች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ ላይም እየሰራ መሆኑን ሚንስትሯ ተናግረዋል፡፡


ኢትዮጵያ በቂ የሰው ኃይል እና የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም በአግባቡ እየተጠቀመችበት አይደለም ይህ ቢስተካከል ችግሩን በራስ አቅም መፍታት ይቻል ነበር ሲሉ ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡


ለ3 ዓመት ይቆያል የተባለው ዘመቻ አፍሪካ ውስጥ በሚተገበሩት ሶስቱ አካባቢዎች የሚታየውን ህፃናት ረሃብና ያልተመጣጠነ ምግብ ችግርን መቅረፍ ዋነኛ ትኩረቱ መሆኑን ተነግሯል።


አፍሪካ ውስጥ በየጊዜው የሚነሳው ጦርነትና ድርቅ ችግሮቹ እንዲባባሱ አድርጓል ተብሏል፡፡


ፕሮግራሙ በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ27 ሀገራት ይተገበራል የተባለ ሲሆን ለየትኞች ሀገራት ምን ያህል ድርሻ እንዳላቸው ግን አልተብራራም።


አሁን ይፋ ፈተደረገው ዘመቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲተገበር የትምህርት ቤት ምገባ ትኩረት እንደሚሰጠው ሰምተናል፡፡



በረከት አካሉ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



Comments


bottom of page