top of page

የካቲት 13፣2016 - የራዳር መሳሪያ እጥረት ለስራው ፈተና እንደሆነበት የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ተናገረ

የተሽከርካሪዎችን የፍጥነት ወሰን ለመቆጣጠር የሚያግዘውን የራዳር መሳሪያ እጥረት ለስራው ፈተና እንደሆነበት የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ተናገረ፡፡


ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሸገር እንደተናገረው የትራፊክ አደጋን ከሚፈጥሩ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እንደሆነ ይነገራል፡፡


ባለበት የሰው ሃይል እና የራዳር መሳሪያዎች እጥረት ምክንያት የፍጥነት ወሰን ቁጥጥር የሚሰራው አልፎ አልፎ መሆኑን የተናገሩት በባለስልጣኑ መስሪያ ቤቱ የዲጂታል ሚዲያ ባለሞያ የሆኑት አቶ መኳንንት ምናሴ ናቸው፡፡


ከሰሞኑ በሁለት ክፍለ ከተሞች ለ2 ሰዓታት ብቻ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ከ325 በላይ ሰዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ ተገኝተው እርምጃም ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡


የፍጥነት ወሰን የቁጥጥር ባለሞያዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች፤ አሽከርካሪዎች በአብዛኛው በፍጥነት እንደሚያሽከረክሩ የነገሩን አቶ መኳንንት ያለብንን የሰው ሃይል እጥረትን ለመቅረፍ በቅርቡ 400 ሰራተኞችን ለመቅጠር ተሰናድተናል እንዲሁም የመንገድ ካሜራዎችን በመግጠም ለመቆጣጠር አስበናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


በሌላ በኩል የፍጥነት ወሰንን ለመገደብ በየመንገዱ የተሰራውና በአሽከርካሪዎች ዘንድ ቅሬታ የሚነሳበትን በኮንክሪት የሚሰራውን የፍጥነት መገደቢያ እያስቀረን በጎማ እየቀየርነው ነው፤ መገደቢያዎቹ ሲገነቡ አለም አቀፍ ደረጃዎችን አሟልተው ነው ብለዋል፡፡


በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ5,000 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ይሞታሉ ተብሏል፡፡


ከሟቾች መካከልም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት እግረኞች መሆናቸውንም ሰምተናል፡፡



ምንታምር ፀጋው




የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



コメント


bottom of page