በኢትዮጵያ ለዓመታት የዘለቀው የሰላም እጦት እና የንፁሀን ሞት አስጨንቆናል በማለት፤ የተለያዩ አካላት ለመንግስት እና በተቃርኖው ለቆሙት የሰላም አውርዱ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
በተለያዩ መድረኮች የሰላም ጥሪ ከሚያቀርቡት መካከል ‘’የገዳይም የሟችም እናት እኔው ነኝ’’ በማለት የሚታወቁት የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች ማህበር አንዱ ነው፡፡
እነዚህ እናቶች የሰሜኑ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ወደ #መቀሌ ሄደው ‘’እርቅ ይውረድ’’ ብለው ተማጽነው እንደነበረም ይታወቃል፡፡

የእናቶች ማህበሩ ለዓመታት ያደረኩት የሰላጥሪ በሚፈለገው ልክ ውጤት ባያመጣም አሁንም ለመንግስትም ሆነ ለታጣቂዎች የሰላም ጥሪ ማቅረቤን አላቆምም፤ ተስፋም አልቆርጥም ሲል ነግሮናል፡፡
በሀገሪቱ #ሰላም እንዲወርድም ‘’በመጀመሪያ መኖሪያችሁ በሆነው ማህጸናችን፤ በመጀመሪያ ምግባችሁ በሆነው ጡታችን’’ በማለት ተማጽነዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች ተወካይ ወ/ሮ መዓዛ በቀለ ‘’በ1997 ዓ.ም የነበረው ሁኔታ አስገድዶን የጀመርነው የሰላም ጥሪ ዛሬም ቀጥለናል’’ ብለውናል፡፡
የሰላም ጥሪያችሁን እንዴት ባለ መልኩ ነው የምታቀርቡት ያልናቸው ወ/ሮ መዓዛ አብዛኛውም ጊዜ የሀይማኖት አባቶችን እንደሚጠቀሙ ነግረውናል፡፡
ከእርስ በዕርስ መገዳደል ጀምሮ ለሰላም እጦት ምንያት የሚሆኑ በርካታ ችግሮች በኢትዮጵያ እንዳሉ የሚጠቅሱት የሰላም እናቶች ተወካይ ‘’እኛ እናቶች ፍርሀታችን እና እንባችን ብዙ ነው፤ ለዚህም ነው ለሰላም የምንጣራው’’ ይላሉ፡፡
እነዚህ ከተለያየ ቦታ የተሰባሰቡ እናቶች የሰላም ጥሪ ለ20 ዓመታት ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ ለመሆኑ ያመጡት ውጤት ይኖር ይሆን? ጠይቀናል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments