የካቲት 12 2017 - በኮሪደር ልማት ምክንያት ከግል ይዞታቸው ለተነሱ ነዋሪዎች ከ9.5 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተናገረ
- sheger1021fm
- Feb 19
- 2 min read
በኮሪደር ልማት ምክንያት ከግል ይዞታቸው ለተነሱ ነዋሪዎች ከ9.5 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተናገረ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት በ4ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤው፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባቀረቡት የ6 ወር ሪፖርት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል በከተማዋ እተከወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ አንዱ ነው፡፡
ሁለተኛው ዙር ኮሪደር ልማት የሌሎች ሃገራትን ተሞክሮ በመውሰድ በፍጥነት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በአጠቃላይ 3ሺህ 515 ሄክታር ቦታን በሚሸፍነው የኮሪደር ልማት ከግል ይዞታቸው ለተነሱ ነዋሪዎች ከ9.5 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል፤የቀበሌ ነዋሪዎች ለነበሩት ደግሞ 9 ሺህ ቤቶች ቀርቦላቸዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም 1402 የመስሪያ ቦታዎችን፣200 የንግድ ሱቆችን በምትክ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ያሉት ከንቲባዋ ተያዘለት ያሉት ጊዜ መቼ እንደሆነ አልጠቀሱም፡፡

ባለፉት 6 ወራት በከተማዋ በተሰበሰበው የገቢ ግብር 111.5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን በሪፖርፖርታቸው የጠቀሱት ከንቲባዋ የተገነው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር የ50 በመቶ ብልጫ አለው፤ ይህም ሆነው የታክስ መሰረትን በማስፋትና ህግን ማስከበርን በመቻላችን እንጂ የጨመርነው የታክስ አይነት የለምም ብለዋል፡፡
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በ2017ዓ.ም ተከመደበው የ5.4 ቢሊዮን ብር በጀት 71 በመቶውን ለዘላቂ ልማት፣ድህነትን ለመቅረፍና የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እንደዋለም ጠቁመዋል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችን ለመደገፍ ተጨማሪ 12 ቢሊዮን ብር ተመድቦ ለተማሪዎች ምገባና የምግብ ቁሳቁስ ለሟሟላት፣ ለትራንስፖርትና ለጤና መድህን አገልግሎት እየዋለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በኮሪደር ልማቱ ከመኖሪያቸው ለተነሱ የቀበሌ ቤት ነዋሪ ለነበሩ ሰዎች 9 ሺህ ቤት ቀርቦላቸዋል ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ በሌላ በኩል ከግል ይዞታቸው ለተነሱት ደግሞ ከ9.5 ቢሊዮን ብር በላይ ካሣ ተከፍሏል ብለዋል፡፡
ለ2017 አመት ከፌዴራል በጀት ለከተማዋ የተደለደለው የድጎማ በጀት ከ5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እምብዛም የማይበልጥ ሲሆን ባለፉት 6 ወራት ደግሞ 111 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቢያለሁ ብሏል፡፡
በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ የሚያስከፍለው የጣሪያና የግድግዳ ግብር በፍርድ ቤት መሻሩን በመጥቀስ አንድምታው ምንድነው? የሚል ጥያቄም ለከንቲባዋ ቀርቦላቸዋል፡፡
ለግል ባለይዞታዎችም ለልማት ተነሺዎች የሚሰጠው ካሣስ አሁን ካለው የግንባታ ዋጋ ውድነት አንፃር የሚያስገነባ ነው ወይ? የሚሉና ከፍተኛ ወጭ እየጠየቀ ያለው የኮሪደር ልማት በጀት ምንጩ ከየት ነው የሚል ጥያቄም ከምክር ቤቱ አባላት ቀርቧል፡፡
ሌሎችም ጥያቄዎች እየቀረቡ ሲሆን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምላሽ ይሰጡባቸዋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments