ወሩ የካቲት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በጥናታዊ ፅሁፍ፣ በውይይት እና በምክክር የ1966ቱ አብዮት 50ኛ ዓመት ለ1 ዓመት ለመዘከር መታሰቡ ተሰማ፡፡
ይህ የተነገረውየማህበራዊ ጥናት መድረክወይንም ፎረም ፎር ሶሻል እስተዲስ ለመገናኛ ብዙሃን ትላንት በሰጠው መግለጫ ነው፡፡
ዝክረ አብየቱ ለ1 ዓመት ይቆያል የተባለ ሲሆን በየ 2 ወር የሚካሄድ ነው፡፡
ይህም ከየካቲት 2016 እስከ የካቲት 2017 ይቆያል ተብሏል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዳይሬክተር ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ተማሪዎች፣ ሰራተኞች፣ ታክሲ አሽከርካሪዎች፣ ወታደሮች እና የተለያዩ የተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎች በ1966 ዓ.ም በየካቲት ወር የተጀመረው አብዮት ምን አመጣ? ምን አጎደለ? የሚለው በአዋቂዎች ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦበት ውይይት ይካሄድበታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካዊና በተለይም የሽግግር ፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭቶች መስፋፋት የአብዮቱን 50 ዓመት ጉዞ መፈተሽ አስፈላጊ ያደረገው አንዱ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ለ1 ዓመት የሚዘልቀው ምክክር ከየካቲት እስከ የካቲት በሚል ርዕስ የፖሊሲ ፋይዳ ባላቸው ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር 6 የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት የአብዮቱን 50 ዓመት ለመዘከር ታቅዷል፡፡
የእነዚህ ውይይቶች ዓላማ ወደ ኋላ ተመልሶ የአብዮቱን ዘመን ክርክሮች ለመድገም ሳይሆን የሰከነ ምሁራዊ ውይይቶችን ለማድረግ ነው ሲሉ ዶ/ር የራስወርቅ አስረድተዋል፡፡
እንደመነሻም እረጅሙን የ50 ዓመት ጉዞ ከአብዮቱ ዓላማ አንፃር እንዴት ይታያል?
የአብዮቱ ትውልድ ጥያቄዎች ዛሬ ከ50 ዓመት በኋላ የት ደረሱ? ሀገሪቱንስ ወዴት አቅጣጫ ወሰዷት?
የሚነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ከዛሬ 50 በፊት ከተነሱት ምን ያህል ይዛመዳሉ? ይለያያሉ?
ከአብዮቱ ዘመን በተለይ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ክርክሮች ምን ተሞክሩ መውሰድ ይቻላል?
የመጪው 50 ጉዞ እንዴት ይታያል? በሚሉ ጥያቄዎች ላይ ውይይት እና መዘክር እንደሚደረግባቸው ሰምተናል፡፡
ከእነዚህ ጥያቄዎች ስር የመሬት ጉዳይ፣ የማንነት፣ በተለይም የብሔር፣ የሃይማኖትና ፆታ ጥያቄዎች የሰራተኛ ጉዳዮች፣ የአለም አቀፍ ግንኙነቶች እንዲሁም የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ የውይይቱ ዋነኛ የውይይት ርዕሶች ይሆናሉ ያሉት ደግሞ የፖለቲካን ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶ/ር ዮናስ አሽኔ ናቸው፡፡
የውይይቱ ዓላማ በአብዮቱ ጊዜ የነበሩ ምሁራን ትዝታቸውን እንዲያካፍሉ ሳይሆን ወይንም ከማለፋቸው በፊት አንድ እድል ለመስጠት ታስቦ ሳይሆን ሀገርን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመምከር የተሰናዳ እንደሆነ በመግለጫ ላይ ሲነገር ሰምቷል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments