የካቲት 11 2017 - የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጠኝን ስራ በተሰጠኝ ጊዜ ውስጥ ሰርቼ ጨርሻለሁ አለ
- sheger1021fm
- Feb 18
- 1 min read
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጠኝን ስራ በተሰጠኝ ጊዜ ውስጥ ሰርቼ ጨርሻለሁ አለ፡፡
ኮሚሽኑ ይህን ያለው የ3 ዓመት የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
የኮሚሽኑ የስራ ክንውን ሪፖርት ለምክር ቤት አባላት በንባብ ያቀረቡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3 ዓመት ውስጥ እንድናከናውን የሰጠንን ሀላፊነት ሰርተን ጨርሰናል ብለዋል፡፡
#የሀገራዊ_ምክክር _ኮሚሽን እስካሁን በ10 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ መሰብሰቡ ይታወቃል፡፡
ይሁንና ኮሚሽኑ በአማራና በትግራይ ክልሎች እስካሁን አጀንዳ እንዳልሰበሰበ የሚታወቅ ቢሆንም ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት ግን ምክር ቤቱ በ3 ዓመት ውስጥ እንድናከናውን ያዘዘንን ስራ ሰርተን ጨርሰናል ብለዋል፡፡
ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በሪፖርታቸው ባለፉት 3 አመታት በርካታ ችግሮች ቢገጥሙንም በ10 ክልሎችና በ2 ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ መሰብሰብ ችለናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ከ1260 በላይ የአጀንዳ ሰነዶችን ተረክበናል ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን በብሔራዊ ደረጃ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የምክክር ምዕራፍ እስካሁን 1105 ተወካዮች መመረጣቸውንም አስታውሰዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት 3 ዓመታት ከ1.3 ቢሊዮን በላይ ገንዘብ ማግኘቱን የተናገረ ሲሆን ከዛም ውስጥ የተጠቀመው ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በፀጥታ ችግር፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አካላት እንዲሁም አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክክር ምዕራፍ አለመግባታቸው ያለፉት 3 ዓመታት ጉዞዬ አስቸጋሪ አድርጎታል ያለ ሲሆን የእነሱ ወደ ምክክሩ መግባት ለምክክሩ ሒደቱ ስኬት ወሳኝ ነው ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተሰጠው የሶስት ዓመት የስራ ጊዜ የፊታችን አርብ የካቲት 14 የሚያበቃ የነበረ ሲሆን ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ዓመት ተጨማሪ እድሜ ተሰጥቶታል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Website: https://shorturl.at/yCz7q
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comentarios