top of page

የካቲት 11 2017 ''ብልፅግና የምክክር ኮሚሽንን የመንግስት የአስተዳደር ሥርዓት ከፓርሊያመንታሪ ወደ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ለማሸጋገር ላለው ፍላጎት ማሳኪያ መሳሪያ ሊያደርገው መሆኑ ይነሳል'' የምክር ቤት አባል

ብልፅግና ፓርቲ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የመንግስት የአስተዳደር ሥርዓት ከፓርሊያመንታሪ ወደ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ለማሸጋገር ላለው ፍላጎት ማሳኪያ መሳሪያ ሊያደርገው መሆኑ በህዝብ ዘንድ ይነሳል ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል ተናገሩ፡፡


ይህን የተናገሩት የምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ(ዶ/ር) ናቸው፡፡


ዶክተር ደሳለኝ ይህንን የተናገሩት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የስራ ዘመኑ የካቲት 14 አርብ ሊጠናቀቅ ለነበረው #የሀገራዊ_ምክክር_ኮሚሽን ተጨማሪ የአንድ ዓመት የስራ ዘመን ለመጨመር እና የሶስቱን ዓመት የስራ ክንውን ሪፖርት ለማዳመጥ በጠራው ስብሰባ ላይ ነው፡፡


በፓርላማው የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የፕሬዘዳንታዊ የአስተዳደር ስርዓት ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል ከተባለ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በአጀንዳነት ይዘን ልናቀርብ እንችላለን ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ምን ያህል ህዝብ የምክክር ሂደቱን ህጋዊ ነው ብሎ ያምናል? ለደረቅ #ፕሮፓጋንዳ ሲባል እንደ ዓይኑ ብሌን ነው የሚጠብቀው ልንል እንችላለን ወይ? ግን ደግሞ ሰፊ ጥርጣሬ እንዳለ መካድ የለብንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡


በዋንኛነትም ብልፅግና የሆኑ የፖለቲካ አላማዎቹን ለማሳካት የሚጠበቅበት በግልፅ እንደሚነገረው ላንሳ የመንግስት የአስተዳደር ስርዓቱን ከፓርላሜንታዊ ወደ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ለማድረግ የሚፈለገውን ሽግግር ማስኬጃ መሳሪያ ነው ተብሎ በህዝብ ዘንድ ይነሳል ብለዋል፡፡


ስለዚህ በአግባቡ ለህዝብ ማስረዳት መቻል አለብን ሲሉ ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡


በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚንስትር የሆኑት ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው እንደራሴው ላነሱት ሃሳብ በሰጡት መልስ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ አሁን እያነሱ ያለው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሆይ ፍጠኑ ነው የሚለው ሲሉ አስረድተዋል፡፡


በህዝብ ዘንድ ኮሚሽኑ ቅቡልነት አለው ያሉት ዶክተር ተስፋዬ ነገር ግን የተወሰኑ አካላት ቅቡልነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ አሉ ሲሉ ከሰዋል፡፡


ብልፅግና ለሀገራዊ ምክክር እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ይዞ የሚቀርባቸው የራሱ #አጀንዳዎች አሉት ያሉት ዶክተር ተስፋዬ ወቅቱ እና ጊዜው ሲደርስ ይቀርባል ብለዋል፡፡


ብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ለዚህ ሃገር ያስፈልጋል ከተባለ ይዘን ልንቀርብ እንችላለን ምን ችግር አለው? ምን የሚያስፈራ ነገርስ አለው? ሲሉ ተደምጠዋል፡፡


ኮሚሽኑ በህዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በተለያዩ አካባቢዎች የተመለከትነው ህዝብ በኮሚሽኑ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳለው ነው ብለዋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page