top of page

የካቲት 11፣2016 - በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ 6 አባል ሀገራት ከአባልነት መታገዳቸው ተሰምቷል

የአፍሪካ ህብረት 37ተኛው የመሪዎች እና 44ተኛው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዶ ትናንት ምሽት መጠናቀቁ ታውቋል፡፡


በዚህ ስብሰባ ስድስት የአህጉሩ አባል ሀገራት ከአባልነት መታገዳቸው ተሰምቷል፡፡


በአህጉሩ የሚታየው የሰላምና የፀጥታ ችግር እንዲሁም ኢ-ህገ መንግስታዊ የስልጣን ለውጥ ለሀገራቱ መታገድ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል፡፡


የህብረቱ የሰላምና የፀጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ ህብረቱ ጋቦን፣ ኒጀር፣ ጊኒ፣ ሱዳን፣ ቡርኪናፋሶ እና ማሊን ከአባልነት ማገዱን ተናግረዋል፡፡


ትናንት ምሽት ከተጠናቀቀው የመሪዎች ጉባኤ ቀደም ብሎ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ይታወሳል፡፡


ከእነዚህ መካከል አርብ እለት አዲስ አበባ የደረሱት እና ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የሶማሌያው ፕሬዘዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ አንዱ ሲሆኑ ተጉላላሁ በሚል ሰበብ ፕሬዘዳንቱ ስብሰባውን አቋርጠው ቅዳሜ እለት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተሰምቷል፡፡


ፕሬዘዳንቱ እና ልዑካቸው የመሪዎቹ ስብሰባ በተጀመረበት እለት ከሆቴላቸው ለመውጣትና ወደ ህብረቱ አዳራሽ ለመግባት በሞከሩበት ወቅት በታጠቁ የፀጥታ አካላት መከልከላቸውን በተመለከተ ጉባኤውን ከተሳተፉ በኋላ ፕሬዘዳንቱ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡


የኢትዮጵያ መንግስት በኮሚኒኬሽን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ በኩል በሰጠው መግለጫ የፕሬዘዳንቱን ክስ አስተባብለዋል፡፡


ኢትዮጵያ የዝግጅቱ አስተናጋጅ እንደመሆኗ ለእንግዶች ደህንነት ሀላፊነት እንዳለባት በመግለፅ የሶማሌያ ልዑካን ቡድን በመንግስት የተመደበላቸውን የፀጥታ ሰራተኞች አንቀበልም ማለታቸውን እና በተጨማሪም የፕሬዘዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ጠባቂዎች መሳሪያ ታጥቀው ወደ ህብረቱ ቅጥር ግቢ ለመግባት በሞከሩበት ወቅት በህብረቱ የፀጥታ አካላት መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያ መንግስት የፕሬዛንቱንና የልዑካቸውን ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር በስብሰባው ላይ እንዳይገኙ እና ህብረቱ ግቢ እንዳይገቡ አልከለከለም ሲሉ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል፡፡


ፕሬዘዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ስሞታ ካሰሙ እና ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሀገራቸው የውጪ ጉዳይ መ/ቤት ሁኔታው የዲፕሎማሲ እና አለም አቀፍ ደንብን የሚጥስ በመሆኑ የአፍሪካ ህበረት ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ የህብረቱ መቀመጫ ያለበትን ሀገር ሁኔታ ማጤን ሊያስፈልገው ይችላል ሲል መግለጫ ማውጣቱ ተሰምቷል፡፡


ፕሬዘዳንት ሼክ ሀሰን ወደ አዲስ አበባ የመምጣታቸውን ጉዳይ ከመነሻው በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ለመቃወም እና የህብረቱ መሪዎችም እንዲቃወሙ ለማስተባበር እንደሆነ በህብረቱ ስብሰባ ላይ ተናገረዋል፡፡


ፕሬዘዳንት ሀሰን ሼክ የህብረቱን 37ኛ የመሪዎች የመዝጊያ ፕሮግራም ሳይካፈሉ ወደ ሀገራቸው ቅዳሜ ምሽት መመለሳቸው ታውቋል፡፡


የህብረቱ ጉባኤ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መ/ቤት ተናግሯል፡፡የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


bottom of page