የባህርማዶ ወሬዎች - ሰኔ 3 2017
- sheger1021fm
- Jun 10
- 2 min read


የደቡብ ሱዳኗ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አንጀሊና ቴኒ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶቻቸው በመንግስት የፀጥታ ባልደረቦች ተወሰዱባቸው፡፡
ከአንጄሊና ቴኒ መኖሪያ ቤት ከተንቀሳቃሸ ስልካቸው በተጨማሪ ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተራቸው እና ለኢንተርኔት ግንኙነት የሚገለገሉበት ሞደም መወሰዱን ሬዲዮ ታማዙጅ በድረ ገፁ ፅፏል፡፡
አንጀሊና ቴኒ የአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ሪያክ ማቻር ባለቤት ናቸው፡፡
እሳቸውም እንደ ባለቤታቸው ከቁም እስር ያልተለየ ሕይወት እየገፉ ነው ተብሏል፡፡
በደቡብ ሱዳን ዳግም ፖለቲካዊ ቀውሱ እየተባባሰ ከመጣ ወራት አስቆጥሯል፡፡
የአለማችን ተፅዕኖ አሳዳሪ አገራት የደቡብ ሱዳን መንግስት ማቻርን እና የፖለቲካ የቅርቦቻቸውን ከእስር እንዲፈታቸው እየጎተጎቱ ነው ተብሏል፡፡
***********
ዘመዶቻቸው በሐማስ የታገቱባቸው እስራኤላውያን የአገራቸው መንግስት የጋዛ የጦር ዘመቻውን እንዲያቆም ጠየቁ፡፡
የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣ በታጋቾቹ ዘመዶች እና አጋሮቻቸው በሰልፍ የተጠየቀው በቴል አቪቭ የሊኩድ የፖለቲካ ማህበር ፅህፈት ቤት አካባቢ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ሰልፈኞቹ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ለቅቆ ቢወጣ በጋዛ የቀሩ ታጋቾች በሙሉ እንደሚለቀቁ ያምናሉ ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ56 ያላነሱ ታጋቾች በሐማስ እጅ ይገኛሉ፡፡
ከመካከላቸው 20ዎቹ በሕይወት እንዳሉ እንደሚገመት በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
እስራኤል ዳግም የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ከጀመረች ከ3 ወራት በላይ ሆኗታል፡፡
ከዚያን ጊዜ አንስቶ የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥ ተደርጎ አያውቅም፡፡
***********
በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛታዊ አስተዳደር ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ሊከሳቸው ነው፡፡
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒሶን ፕሬዘዳንት ትራምፕን እንደሚከሷቸው እወቁልኝ ማለታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የካሊፎርኒያ ግዛታዊ አስተዳደር ትራምፕን የሚከሳቸው በሎስ አንጀለስ ብሔራዊ ዘብ የተሰኘውን የፌዴራል ሰራዊት ወታደሮች በማሰማራታቸው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
በሎስ አንጀለስ የስደተኞችን እየታሰሩ መባረር የሚቃወም ሰልፍ ተጠርቶ ነበር፡፡
ግዛታዊ አስተዳደሩ ነገሩ ከአቅሜ በላይ ሳይሆን ትራምፕ ብሔራዊ ዘቡን ማሰማራታቸው ህገ-ወጥም የስልጣን ገደብንም መተላለፍ ነው ብሎታል፡፡
ትራምፕ በፊናችሁ ያላችሁትን በሉ እንጂ እርምጃዬ ህጋዊ እና ትክክለኛ ነው እያሉ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
ፕሬዘዳንቱ ተጨማሪ 2 ሺህ የፌዴራል ብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ወደ ሎስ አንጀለስ እየላኩ ነው ተብሏል፡፡
***********
ሩሲያ እና ዩክሬይን የጦር ምርኮኞችን መለዋወጥ ጀመሩ፡፡
የጦር ምርኮኞች ልውውጥ ባለ ብዙ ምዕራፎች ሆኖ የሚከናወን ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ የምርኮኞች ልውውጥ ሁለቱም አገሮች እድሜያቸው ከ25 አመት በታች የሆነ ምርኮኞችን መለዋወጣታቸው ተሰምቷል፡፡
የጦር ምርኮኞቹ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን የሁለቱም አገሮች መንግስታት ማረጋገጣቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ባለፈው ሳምንት የሁለቱ አገሮች ወሰን ተሻጋሪ ጥቃት ተባብሶ መሰንበቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
በተለይም ሩሲያ ቀደም ሰል በአየር ሀይል ሰፈሮቿ ላይ በዩክሬይን ለተፈፀመባት ሰርጎ ገብ የድሮን ጥቃት ምላሿ የከፋ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ይህም የጦር ምርኮች ልውውጡ አስቀድሞ ከታቀደው ጊዜ እንዲዘገይ አድርጓል ተብሏል፡፡
ሁለቱ አገሮች የጦር ምርኮች ልውውጥ የሚያደርጉት ቀደም ሲል በቱርክ ኢስታምቡል በደረሱት ስምምነት መሆኑ ታውቋል፡፡
***********
በጀልባ ተጓጉዘው ወደ ጋዛ ሰርጥ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ አልመው የነበሩት በጎ ፈቃደኞች ተልዕኳቸው በእስራኤል ባህር ሀይል ተጨናግፎ በቴል አቪቭ በኩል ወደየአገሮቻቸው ተገድደው ሊላኩ ነው ተባለ፡፡
በጎ ፈቃደኞቹን አሳፍራ ወደ ጋዛ በማምራት ላይ የነበረችው ጀልባ በእስራኤል አሸዶድ ወደብ መልሕቋን እንድትጥል መደረጓ ታውቋል፡፡
በጀልባዋ ወደ ጋዛ በማምራት ላይ ከነበሩ 12 በጎ ፈቃደኞች መካከል ስዊዲናዊቷ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ግሬታ ተምበርግም አንዷ ነበረች ተብሏል፡፡
በእስራኤል ሀይሎች ተይዘው የሚገኙት በጎ ፈቃኞቹ ወደ አገራቸው ለመላክ ወደ ቤንጉሪዮን ኤርፖርት መወሰዳቸውን የእስራኤል ሹሞች ተናግረዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞቹ ከዓለም አቀፍ የውሃ አካል በእስራኤል ሀይሎች ታግተናል በሚል እያማረሩ መሆኑን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
Comments