top of page

የሐምሌ 20 የውጭ ሀገር ወሬዎች

  • Jul 27
  • 2 min read


በቀይ ባህር የባብኤል መንደብ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦች ብዛት በእጅጉ እየቀነሰ ነው ተባለ፡፡


በወሽመጡ የሚተላለፉ መርከቦች ብዛት የቀነሰው የየመን ሁቲዎች ባለፈው ሳምንት የሳውዲ አረቢያን ወደቦች እንከቻችምባታለን ብለው ከዛቱ በኋላ እንደሆነ ሬውተርስ ፅፏል፡፡


ለምሳሌም ትናንት በባብኤል መንደብ የባህር ወሽመጥ በኩል ያለፉት የጭነት መርከቦች 11 ብቻ እንደሆኑ የባህር ጉዞ መረጃ አጠናቃሪው የኬፕለር መረጃ ያሳያል፡፡


ይሄም በወሩ በባብኤል መንደብ ወሽመጥ ከተላለፉት መርከቦች ብዛት እጅግ ዝቅተኛው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


የየመን ሁቲዎች እና ሳውዲ አረቢያ ዳግም ወደ ጦር ፍጥጫቸው ከተመለሱ ሰንብተዋል፡፡


ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ የየመንን አብዛኛውን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የፖለቲካ ሸሪኮች እና የጦር አጋሮች እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡




ፈረንሳይ በከፍተኛ የሰደድ እሳት እየተፈተነች ነው ተባለ፡፡


የአገሪቱ የእሳት አደጋ ተከላካዮች በቦርዶ ከተማ አቅራቢያ ከተቀሰቀሰ የሰነበተው ከባድ የሰደድ እሳት መዛመት ለመከላከል በትግል ላይ እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ብቻ ከአካባቢው 55 ሺህ ያህል ነዋሪዎችን ማስወጣታቸው ተነግሯል፡፡


በፈረንሳይ ደቡባዊ ምዕራብ የሰደድ እሳቱ በ98 ሺህ ሄክተር መሬት ላይ የነበረን ደን እና ቁጥቋጦ ማውደሙ ታውቋል፡፡


በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይን የገጠማት ታላቅ የሰደድ እሳት ከ2ኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ውድመት አስከትሎባታል ተብሏል፡፡


ስፔንም በከባድ የሰደድ እሳት እየተፈተነች ነው፡፡


የሰደድ እሳቱ በፈረንሳይ እና ስፔን እስካሁን ከ330 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀሉን መረጃው አስታውሷል፡፡




የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ዩክሬይን በካስፒያን ባህር በንግድ መርከባችን ላይ ለፈፀመችው ጥቃት የእጇን እንሰጣታለን አሉ፡፡


በጥቃቱ አንድ ኢራናዊ ባህረኛ መገደሉን አራግቺ በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ባሰፈሩት መልዕክት እወቁልን ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


በዚሁ ጥቃት በሌላ ኢራናዊ ባህረኛ ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል፡፡


የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በካስፒያን ባህር አርቀን የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ ቁሳቁስ ማጓጓዣ መርከብ ላይ ያነጣጠረ የተሳካ ጥቃት አድርሰናል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩክሬይን በእስራኤል አባሪ ተባባሪነት በጭነት መርከባችን ላይ ጥቃት በማድረስ አውሮፓን ወደ ጦርነቱ እየሳበች ነው ሲሉ ጥቃቱን በፅኑ አውግዘዋታል ተብሏል፡፡


መስሪያ ቤታቸውም በኢራን የዩክሬይን ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚውን በማስጠራት ተቃውሞውን ማቅረቡ ተጠቅሷል፡፡




አሜሪካ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በኢራን ላይ ስትፈፅም የሰነበተችውን ድብደባ ገትታዋለች ተባለ፡፡


ኢራንም ወደ አቅራቢያው አገሮች ስታደርስ የነበረውን አፀፋ ድብደባ ማቆሟን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


አሜሪካ የኢራን ድብደባዋን የገታችው በገጠማት ከፍተኛ የተተኳሾች እጥረት የተነሳ ነው መባሉን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይሄ በፍፁም ሐሰት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ከበቂ እና አስፈላጊ በላይ የተተኳሾች ክምችት አለን ብለዋል ፕሬዘዳንቱ፡፡


የተለያዩ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የአገሪቱ ጦር ከፍተኛ ተተኳሾች እጥረት እንደገጠመው ቀደም ብለው እየተቀባበሉ መዘገባቸው ተጠቅሷል፡፡


የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ አሜሪካ ቀዳሚውን ስምምነት በመጣስ ክህደት ብትፈፅምም አሁንም በአደራዳሪዎቹ በኩል ከአሜሪካ ጋር የመልዕክት ልውውጥ እያደረግን ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


አሜሪካ በፊናዋ የጦርነት ማስቆሚያውን የመግባቢያ ስምምነት የጣሰችው ኢራን ነች በሚል ክሷ እንደገፋችበት መረጃው አስታውሷል፡፡



የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
የነሐሴ 9 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ኮንጎ የኮንጎ ኪንሻሣው የኢቦላ ወረርሽኝ አድማሱን እያሰፋ ነው ተባለ፡፡ ወረርሽኙ ወደ ተጨማሪ ግዛትም መዛመቱን የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ /አፍሪካ CDC/ መረጃ ማሳየቱን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡ በኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ያዳረሳቸው ግዛቶች ብዛት 6 ደርሷል፡፡ ኢቱሪ ወረርሽኙ ከፍተኛ ጫና ያሳደረ

 
 
 
የነሐሴ 8 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#የተባበሩት_አረብ_ኢሚሬትስ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በሆርሙዝ ወሽመጥ በሁለት መርከቦቼ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ያለቻትን ኢራንን በብርቱ ኮነነቻት ተባለ፡፡ ኢራን በነዳጅ ጫኝ መርከቦቻችን ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ሲል ከበድ ያለ ተቃውሞውን ያሰማው የኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሆነ አልጀዚራ እና AFP ፅፈዋ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page