top of page

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ለዋናው የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አስር አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ ያደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  • Jun 24
  • 3 min read

ሰኔ 17/2018

 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ለዋናው የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አስር አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ ያደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


የምክክር ኮሚሽኑ ይፋ የሚደርጋቸው አጀንዳዎች ለዋና ጉባዔ ማለትም ሃምሌ 8 ቀን 2018ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባዔ ላይ ቀርበው የሚመከርባቸው ናቸው፡፡


ለዋናው ጉባኤ የፌደራል መንግስት ተወካዮችን ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተወከሉ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትን ጨምሮ ከ4 ሺህ በላይ ጉባዔተኞች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


ኮሚሽኑ ዛሬ ይፋ የሚደርጋቸው አጀንዳዎች ከትግራይ ክልል ውጪ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እና በሁሉም ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ ከተለያዩ የህብረተስብ ከፍሎች ከተሰበሰቡ በሺዎች ከሚቆጠሩ አጀንዳዎች ውስጥ ኮሚሽኑ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ለአገሪቱ ችግር መሰረት ናቸው ተብለው የተለዩትን አስር አጀንዳዎች ነው፡፡


ዛሬ ይፋ የሚደረጉት አስሩ አጀንዳዎች የተለዩት ደግሞ በአስር መስፈርቶች ነው ተብሏል፡፡


በዚህም መሰረት አዲስ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር መቻላቸው ታውቆ ፣የህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸው ታምኖበት፣ በአገሪቱ ሲንከባለሉ ለዘመናት የመጡ ችግሮችን የሚፈቱ ከሆነ፣ አጀንዳው ቢቀርብ በህዝብ እና በህዝብ መካከል እንዲሁም በህዝብና በመንግስት መካከል ያሉትን ግንኙነቶች የሚሻሽል ከሆነ ነው፡፡


በተጨማሪም ቅቡልነት ያለው ህገ-መንግስት በመገንባት ሂደት መሰረት የሚጥል ከሆነ ፣አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት ከረዳ ፣ለአገራዊ መግባባት አስተዋጾ የሚደርግ ከሆነ እና የተሸረሸሩ ሀገራዊ እሴቶችን ለማደስ አስዋጾ ካደረገ መሆኑን ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሸነሮች መካከል አንዱ የሆኑት አምባዬ ኦጋቶ አስረድተው ነበር፡፡



የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳድሮች በከወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የተሰበሰቡት 75 በመቶ የሚሆኑት አጀንዳዎች ተመሳሳይነት ያላቸው መሆኑን መናገሩ ይታወሳል፡፡


የፌደራል መንግስት የሀገሪቱ ህገ መንግስት እንዲሻሻል አጀንዳ አድርጎ አቅርቦ የነበረ ሲሆን የክልሎች አወቃቀር ቋንቋ ላይ ሳይሆን አቀማመጥን መሰረት ያደረገ እንዲሆንም ደግሞ የመከላከያ ሰራዊትን አጀንዳው አድርጎ ግንቦት 24 ቀን 2017ዓ.ም በሚሊኒዬም አዳራሽ በተካሄደው የፌደራል ባለድርሻ አካላት አጀንዳ ማሰባሰብ ላይ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡


ታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በተካሄደው እና ከ356 የክልሉ ወረዳዎች የተወከሉ ከ7,000 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በሳተፉበት የጉባዔ ላይ ደግሞ "የኦሮሞ ህዝብ ለ150 ዓመታት ሲጠይቅ የነበረው ጥያቄ"እንዲመለስ የሚሉ አጀንዳዎች ቀርበው ነበር ፡፡


ለምሳሌ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ተጠሪነታቸው ለኦሮሚያ ክልል እንዲሆን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ስር እንዲትተዳደሩ ፣አፋን አሮሞ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን፣ የወሰን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲገኙ እና መሰል አጀንዳዎች ለምክክር ኮሚሽን ቀርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡


ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ለመጀማሪያ ጊዜ ምክከር የተካሄደበት እና አጀንዳዋን የሰጠቸው አዲስ አበባ አስተዳዳር ነበራች፡፡


ለሰባት ተከታታይ ቀናት በዘለቀው የከተማዋ የምክክር እና አጀንዳ ልየታ ላይ ደግሞ የአዲስ የባለቤትነት ጉዳይ መፍትሔ እንዲሰጥ አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ ነበር፡፡


በአጀንዳ ልየታው ተሳትፈው የነበሩት ጠበቃ እና የህግ በለሙያ ወ/ሮ አዲስ መሀመድ አዲስ አበባ ባለቤቷ ማን ይሁን፣ወሰኗ እሰከየት ደረስ ነው፣የስራ ቋንቋዋ ምን ይሁን፣ብሔራዊ ጀግናዋ ማን ይሁን እና መሰል ጉዳይዎች የከተማዋ አጀንዳ ሆነው ለኮሚሽኑ መቅረባቸውን ነግረውን ነበር፡፡



ሰንደቅ አላማ ፣የመሬት ወይንም የወሰን ጉዳይ ፣የአዲስ አበባ በለቤት ጉዳይ ይፈታ እና የህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ይሻሻል የሚሉ አጀንዳዎች ደግሞ ከአማራ ክልል ቀርበዋል፡፡


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ ሃምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ለምክክር ኮሚሽን ከሰጣቸው አጀንዳዎች ውስጥ የራስን መብት በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለው የህመንግስቱ አንቀጽ 39 ክፍል አለመተማመንን የሚፈጠር ስለሆነ እንዲሻሻል ፣የመንግስት የስራ ሃልፊዎች የስልጣን ቆይታ ይገደብ እና አካታች ትርክት ይገንባ የሚሉ አጀንዳዎች መቅረባቸውን የክልሉ ልማት ማህበራት ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን መለሰ በወቅቱ ነግረውናል፡፡


የህገመንግስቱ አንቀጽ 39 እንዳይሻሻል ከሶማሌ ክልል አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ የነበረ ሲሆን የአፋር ክልል ደግሞ አንዲሻሻል የሚጠይቅ አጀንዳ ቀርቧል፡፡


የብሄራዊ ጀግና፣ምልክት ፣ ቋንቋ ፣ትርክት እና የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይዎች ደግሞ ከሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የቀረቡ አጀንዳዎች ናቸው፡፡


ከዚህ ውጭ ያሉ እና ለምክክር ኮሚሽኑ የቀረቡ ማለትም በህዝቦች መካካል አለመተማመንን የሚፈጠሩ ፣በመንግስት እና ህዝብ መካከል ጥርጣሬ የሚመጡ እና የአገሪቱን ሰላም የማያሻሻሉ አጀነዳዎች ለዋናው ጉባዔ አይቀርቡም ተብሏል፡፡


የወሰን እና የይገባኛል ጥያቄዎችም ወደ ክልሎች የሚተላለፉ ይሆናሉ ሲሉ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር፡፡



የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን 93 ከመቶ ከሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ ወይም ከ1234 ወረዳዎች አጀንዳዎችን መሰብሰቡን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) አስረድተዋል፡፡


ኮሚሽኑ በአካል ተግኝቶ አጀንዳ ያልሰበሰበበት ክልል ተግራይ ብቻ ነው፡፡


በትግራይ ተግኝቶ አጀንዳ መሰብሰብ ያልቻለው ደግሞ ከክልሉ የስራ ሃላፊዎች ፍቃድ ባለማግኘቱ እንደሆነ መናገሩ ይታወሳል፡፡


በዚህም ምክንያት ከከልሉ ተወላጆች እና ከአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ሰካይላይት ሆቴል ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም አጀንዳዎችን ሰብስቧል፡፡


እንዚህን ከተለያዩ አካላት የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን አጣርቶ ለዋና ጉባዔ የሚቀርቡ አሰር አጀንዳዎችን ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በአደዋ ሙዚዬም ለህዝብ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡


ያሬድ እንዳሻው

 


 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page