አፄ ኃይለ ስላሴ ሊግ ኦፍ ኔሸንስ/ሸንጐ ታሪካዊ አቤቱታቸውን ያሠሙት የዛሬ 1928 ዓ.ም በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡
- Jun 30
- 2 min read
የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለ ስላሴ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ ለመንግስታቱ ማህበር /ሊግ ኦፍ ኔሸንስ/ ሸንጐ ታሪካዊ አቤቱታቸውን ያሠሙት የዛሬ 1928 ዓ.ም በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡
የፋሽስቶቹ መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ወደ ስልጣን ሲመጣ እንደ ሌሎቹ የአውሮፓ ኃያላን ጣሊያንን፣ ባለ ቅኝ ግዛት ለማድረግ ነጥፎ ኃሳብ አደረበት፡፡
ለዚህ ደግሞ አንድም፣ የጣሊያንን የአድዋ ሽንፈት ቂም፣ በቀል መወጫ፤ በሌላም በኩል የቅኝ ግዛት ረሃቡ ማስታገሻ አድርጐ ኢትዮጵያን መረጣት፡፡
አፄ ኃይል ስላሴ በጄኔቫ፣ የመንግስታቱ ማህበር /ሊግ ኦፍ ኔሽንስ/ አቤት ባሉበት ዘመን የፋሸስቶች፣ ወረራ ስምንተኛ ወሩን አስቆጥሮ ነበር፡፡
አፄ ኃይለ ስላሴ፣ የአገራቸውን አቤቱታ ለማሠማት ወደ ጉባኤው አትሮኖስ እንደቀረቡ በብዛት ወደዛው የገቡ ናቸው የተባሉ የጣሊያን ጋዜጠኞች በፉጨትና በሁከታ ንግግራቸውን አወኩት፡፡ ቱማታ ፈጠሩ፡፡

ንጉስ ነገስቱ ተስፋ አልቆረጡም፡፡ አዳራሹ ፀጥ እስኪልላቸው ታገሱ፡፡
ከወረራው መጀመሪያ፣ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ የፋሽስት ኃይሎች በኢትዮጵያውያን ላይ፣ ያደረሱት ጥፋትና ውድመት ሕሊና ከሚቀበለው በላይ መሆኑን አስረዱ፡፡
ፋሽስቶች ከዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያንን ወታደር ከሲቪል ሳይሉ፤ ሕፃን አዛውንት ሴት ወንድ ሳይለዩ፤ በተከለከሉ የጦር መሣሪያዎችና በመርዝ ጋዝ እየፈጁ መሆኑን በመጥቀስ ፍረዱኝ አሉ፡፡
ፋሽስቶቹ በአገሪቱ ላይ ሞት እያዘነቡባት፣ እንደሆነና ሰውን እየፈጁና ከብቱን እየረፈረፉት፤ ወንዝ አፈሩን፤ ዙሪያ ገባውን እንደመረዙትም ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ፣ እንደ ብዙዎቹ ሉዓላዊ አገሮች የዘመኑ፣ የመንግስታቱ ማህበር /ሊግ ኦፍ ኔሽንስ/ አባል ስትሆን የጋራ ደህንነት ማስጠበቂያ ዋስትና ይሆነኛል ብላ እንደነበርም አስታወሱ፡፡
አንዲት ነፃ የማህበሩ አባል አገር የጉልበተኛ ወራሪ ሰለባ ስትሆን ዝም መባሉ የድርጅቱ ቃል ኪዳን የት ገባ ሲሉም ሞገቱ፡፡
ኢትዮጵያ ፣ የራሷን ዘመናዊ አጥፊና ደምሳሽ መሳሪያ ከምትሠራው ፋሽስት ጣሊያን እኩል ታይታ፤ የጦር መሳሪያ ስንቅና ትጥቅ እንዳታገኝ ያደረጉትን የድርጅቱን ባለ አቅሞች ፍርድ ገምድልነት ያለ አንዳች ማመንታት በንግግራቸው አወገዙ፡፡
ኢትዮጵያ ተራ ጠመንጃዎችን እንኳ እንዳታገኝ ሲደረግ የጣሊያን ሠራዊትና የጦር መሳሪያ ስንቅና ትጥቅ የጫኑ መርከቦች ሲዊዝ ካናልን ሲያቋርጡ ከልካይ ተቆጣጣሪ የሌለባቸው መሆኑን በብርቱ ኮነኑት፡፡
የድርጅቱ አባል አገሮች በቃል ኪዳናቸው መሠረት ኢትዮጵያ ከጉልበተኛ የፋሽስት ወረራ ራሷን እንድትከላከል በመርዳት ቃላቸውን እንዲያከብሩ ጠየቁ፡፡
ታላላቆቹ የሊጉ አባል አገሮች ይሄን ካላደረጉ አንድ ቀን የኢትዮጵያ እጣ እንደሚደርስባቸው በዚያው ንግግራቸው ተነበዩ፡፡ እንዳሉትም ሆነ፡፡ አውሮፓ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ተናጠች፡፡
በዘመኑ አፄ ኃይለ ስላሴ በጄኔቭ ባሠሙት ፀረ ፋሽስት ንግግር ታይም መፅሄት የዓመቱ ታላቅ ሰው ያላቸው መሆኑ በታሪክ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለ ስላሴ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ ለመንግስታቱ ማህበር /ሊግ ኦፍ ኔሸንስ/ አቤቱታቸውን ካሠሙ ዛሬ 90 ዓመት ሆነው ፡፡
በእሸቴ አሰፋ
ሰኔ 23/2018





Wow, it's inspiring to see how Emperor Haile Selassie stood up for his nation at the League of Nations. Speaking of standing up, when I organize school events I love using a stage timer to keep everything on schedule.