top of page

ነሐሴ 9፣2015 - ቁጥጥር ከተደረገባቸው ምርቶች መካከል የተለያየ ጉድለት በተገኘባቸው 40 በሚሆኑት ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል ተባለ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ቁጥጥር ከተደረገባቸው ምርቶች መካከል ምግብና መድኃኒቶችን ጨምሮ የተለያየ ጉድለት በተገኘባቸው 40 በሚሆኑት ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል ተባለ።


ይህንን ያለው ኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የ2015 እቅድ አፈፃፀሙን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ላይ ነው፡፡


6ቱ ምግብና ምግብ ነክ፣ 28ቱ መድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያዎች በተመለከተ፣ ከሀሰተኛ ሰነዶችና ያልታደሰ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ጋር በተያያዘ 1፣ እንዲሁም የመዋቢያ እቃዎች 1 በድምሩ 40 መዝገቦች ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል ተብሏል።


የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አበራ ደነቀ እንዳሉት ከሆነ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 147 የሀገር ውስጥ የምግብ ፋብሪካዎች፣ 813 ምግብ ላኪዎች፣ አስመጭና አከፋፋይ በአጠቃላይ 960 ድርጅቶች መስፈርት በማሟላት የብቃት ማረጋገጫ ወስደዋል።


በዚህም በበጀት ዓመቱ 2 ሺህ 925 የምግብ አይነቶችን መዝግበናል ያሉት ሀላፊው ባለስልጣኑ እስካሁን የመዘገባቸው የምግብ የምርት አይነቶች 12 ሺህ 807 መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡


ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች እና የመድኃኒት ግብአቶች፤ 33 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መሳሪያዎችና ያልተመዘገቡ፣ በጉዞ ወቅት የተበላሹ እና ጊዜያቸው ያለፈባቸው በመሆኑ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገቡ መደረጉንም ጠቅሰዋል።


በሌላ በኩል የመዋቢያ ምርትን በተመለከተ ለ6 የኮስሞቲክስ አምራቾች ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን በ18 ኮስሞቲክስ አስመጪዎች ላይ ደግሞ ስረዛ፣ እገዳና የማስጠንቀቂያ እርምጃዎች መወሰዱን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመግለጫው ተናግሯል።ፋሲካ ሙሉወርቅየሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Website: t.ly/ShegerFM


YouTube: t.ly/SHEGER


コメント


bottom of page